ኢትዮጵያ የመንግስታቱን ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ በምክትል ፕሬዚዳንትነት ትመራለች

70
መስከረም 9/2012 ኢትዮጵያ 74ኛውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ከዴንማርክ ጋር በምክትል ፕሬዚዳንትነት እንደምትመራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ። ሚኒስቴሩ ዛሬ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥቷል። የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ ነብያት ጌታቸው እንዳሉት፤ የተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ ደረጃ የአየር ንብረት ድርጊት ጉባዔን ኢትዮጵያ በምክትል ፕሬዚዳንትነት ትመራለች። የመንግስታቱ ድርጅት ስድስቱ ኮሚቴዎች ስብሰባ እንደ አውሮጳዊያኑ አቆጣጠር እስከ ታህሳስ 2019 መጨረሻ እንደሚካሄድ ይጠበቃል። ኢትዮጵያ በጠቅላላ ጉባዔውና በስድስቱ ኮሚቴዎች ስብሰባዎች ጥቅሟን ባስጠበቀ ሁኔታ ለመሳተፍ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና በኒውዮርክ ቋሚ መልዕክተኛ ጽህፈት ቤት ዝግጅቱ ተጠናቋል። እንደ አቶ ነብያት ገለጻ በጠቅላላ ጉባዔው ከተያዙ 172 አጀንዳዎች መካከል ኢትዮጵያ በ152ቱ ላይ ቅድመ ዝግጅት አድርጋለች። አጀንዳዎቹ በኢትዮጵያ ያለውን ማሻሻያና ወቅታዊ ጉዳዮችን መሰረት በማድረግ በፖለቲካ፣ በማህበራዊና በኢኮኖሚ መስኮች በምትከናውናቸው እንዲሁም ክልላዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችን ከግምት በማስገባት የተዘጋጁ ናቸው። ኢትዮጵያ በስድስት መድረኮች የምትሳተፍ ሲሆን የከፍተኛ ባለስልጣናት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ከነገ መስከረም 10 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ እንደሚካሄድ አቶ ነብያት ተናግረዋል። የዘላቂ የልማት ግቦች የከፍተኛ ባለስልጣናት የፖለቲካ ስብሰባ መስከረም 13 ቀን 2012 ዓ.ም የሚካሄድ ሲሆን ኢትዮጵያ በዘላቂ የልማት ግቦች አፈጻጸምና ተግዳሮቶች ላይ እንደምትመክር ይጠበቃል። እንዲሁም መስከረም 11 በዓለም አቀፍ የጤና ሽፋን፤ መስከረም 15 ቀን 2012 ዓ.ም ደግሞ በፋይናንስ ለልማት የከፍተኛ ባለስልጣናት ስብሰባ ላይም ኢትዮጵያ ትካፈላለች። ኢትዮጵያ ከመንግስታቱ ድርጅት ጋር በመተባበር በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ያለውን የጤና ችግር ለማቃለል "የሰቆጣ ስምምነት" የከፍተኛ ባለስልጣናት መድረክ መዘጋጀቱን የገለጹት አቶ ነብያት ሚኒስቴሩ ከጤና ሚኒስቴር ጋር የጋራ ኮሚቴ አቋቁሞ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል። በተጨማሪም በጉባዔው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ከመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር በጎረቤት አገሮች ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሚዘጋጁ የጎንዮሽ ስብሰባዎችና ከ15 አቻ ሚኒስቴሮች ጋር እንደሚወያዩ ይጠበቃል እንደ ቃል አቀባዩ ገለጻ። በሌላ ዜና በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ በግብጽ የቀረበውን ሰነድ ኢትዮጵያ የማትቀበለው መሆኑን ቃል አቀባዩ አስታውቀዋል። ''በግብጽ የቀረበው ሰነድ የሦስትዮሽ የውይይት አካሄድን ያልተቀበለና እስከ አሁን ድረስ ከነበረው አሰራር ያፈነገጠ ነው'' ብለዋል። የኢትዮጵያን የአሁንና የወደፊት የመጠቀም መብት የማይቀበል፣ ወደፊት በአባይ ውሃ ላይ ያላትን የልማት ዕቅድ የሚገድብ፣ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ አሞላልን በተመለከተ ሂደቱን ውስብስብና አስቸጋሪ የሚያደርግ እንደሆነም አብራርተዋል። ግብጽ ያቀረበችው ሰነድ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ስለሆነ ተቀባይነት እንደሌለው በመጥቀስ። የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ ከሦስቱ አገሮች የተውጣጡ 15 ሳይንቲስቶች የአገራቱን ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ የሰሯቸው ስራዎች የአገራቱን ትብብር ለማጠናከርና ባለፉት ሰባት ዓመታት የተገነባውን መተማመን ለማጎልበት እንዲሁም ለማስቀጠል ስብሰባው ካቆመበት እንዲቀጥል የኢትዮጵያ ፅኑ እምነት እንደሆነም አመልክተዋል። ''የተለያዩ የማይገቡና ባለፉት ሰባት ዓመታት በጋራ የነበረውን የመተማመንና የመተባበር የሦስትዮሽ መንፈስ የሚረብሹ አዳዲስና ጎጂ የተናጠል ጅማሮዎች ሊገቱ እንደሚገባ ኢትዮጵያ በፅኑ ታምናለች'' ነው ያሉት ቃል አቀባዩ። ኢትዮጵያ አሁንም ወደፊትም የትውልድን ፍላጎት ለማሳካት በትብብርና በጋራ ተጠቃሚነት መንፈስ ሉዓላዊ መብቷን በመጠቀም በአባይ ውሃ ላይ ማልማቷን እንደምትቀጥልም አታውቀዋል።                        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም