ለኢትዮጵያዊያን 'መተሳሰብ' ወይስ 'መቻቻል'?

238
አዲስ አበባ ኢዜአ መስከረም 9/2012 የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዘር፣ የቀለም፣ የብሄርና የሌሎች መገለጫዎቻቸውን ልዩነቶች እንደ ውበት በመቁጠር አጊጠውበት በመተሳሰብ ኖረዋል። እነዚህ ልዩነቶቻቸው ሳይከፋፍሏቸውም በአንድ ልብ አንድ አገር ይዘው የውጭ ወራሪ ጠላት አሸንፈው ለዓለም ጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተምሳሌት ሆነዋል፤ ላልይበላ እና አክሱምን የመሰሉ የጥበብ ምስጢራትን አሻራም በቀደምትነት አስቀምጠው የማይሻር ስምና ዝናን አትርፈዋል። ከ80 በላይ ብሔር ብሔረሰቦችን አቅፋ ለዘመናት የዘለቀችው አገር ኢትዮጵያም ብዙ ፈተናዎችን፣ ብዙ ድሎችን እያለፈች ታላቅ ተስፋ ሰንቃ ዛሬ ላይ ለመድረስ በቅታለች። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን ተፈጥሯዊ በሆነው በአገሪቱ ዜጎች ህብረ ብሄራዊና ህብረ ቀለማዊ መገለጫዎች ውስጥ የፖለቲካዊ አመለካከቶች እየገቡ የግጭት መንስኤ ሊያደርጓቸው የሚሞክሩ አዝማሚያዎች ይስተዋላሉ። ለመሆኑ በኢትዮጵያዊያን ዘንድ የዘር፣ የቀለም፣ የብሄርና ሌሎች ልዩነቶች በፖለቲካ አስተሳሰብ ሳይመነዘሩ ምን ትርጉም ይኖራቸዋል? የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ዋና ፀሃፊ ሼኸ ሃሚድ ሙሳ ይህን ይላሉ። "በሃይማኖትም፣ በፖለቲካ አስተሳሰብም፣ በሃይማኖታዊ አመለካከትም፣ በክልልም፣ በዘርም፣ በቀለምም ያሉት ልዩነቶች ለፀብና ለግጭት መንስኤ መሆን የለባቸውም የኣላህ የችሎታው መገለጫ ናቸው ቋንቋችሁና ከለራችሁ መለያየቱ የእኔን የችሎታ ብቃት ከመጠቆም ባሻገር ሌላ ምንም ነገር የለውም።" ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እነዚህ ልዩነቶች በተለያዩ ፖለቲካዊ አስተሳሰቦች እየሰፉ፣ በመካከላቸው ያለውን አንድነት ሲፈታተንና የቀደመ መተሳሰባቸውን ሲያሳሳው እየተስተዋለ ነው። በዚያ ላይ በመገናኛ ብዙሃንና በተለያዩ የመገናኛ አውታሮች ከ'መተሳሰብ' በላይ 'መቻቻል' ሲሰበክና ሲወሳ ይደመጣል። ለመሆኑ በምሁራን እይታ መቻቻል ምንድነው? ዶክተር ወዳጄነህ መሃረነ ይህን ይላሉ"መቻቻል ማለት  እኔና አንተ ልዩነት አለን ግን  እታገስሃለሁ፣ አልደርስብህም፣ አንተም እንዳትደርስብኝ እፈልጋለሁ ቶለሬት ታደርገኛለህ ያለውን ነገር።" "መተሳሰብስ ምን ማለት ነው? ከመቻቻል በምን ይለያል? ለዶክተር ወዳጄነህ የቀረበላቸው ሌላው ጥያቄ ነው። "ከመቻቻል ግን አልፎ ደግሞ መተሳሰብ አለ አሁን እኔ ላንተ ማሰብ እጀምራለሁ፣ ያንተን የጎደለ ነገር ለመሙላት እሞክራለሁ፣ አንተ የኔን የጎደለኝን ነገር ለመሙላት ትሞክራለህ፣ ባንተ ደካማ ጎን እኔ እቆምልሃለሁ፣ በእኔ ደካማ ጎን አንተ ትቆምልኛለህ ይሄ መተሳሰብ ነው።" ብለዋል፡፡ ታዲያ ኢትዮጵያ አሁን ላለችበት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሁኔታዎች ከመቻቻልና ከመተሳሰብ ለማንኛው ቅድሚያ እንስጥ? የሚለው ጥያቄ ሲነሳ መቻቻል የሚለው ቃል እስከ መቼ የሚለውን ሌላ ጥያቄ ማስከተሉ አይቀሬ ነው። ይሁን እንጂ መቻቻል የሚያስፈልገው በመካከላችን ያሉ ሰው ሰራሽ የአመለካከት ልዩነቶች ቀንሰው መተሳሰብ እስክንችል ነው የሚሉት ምሁሩ ዶክተር ወዳጄነህ መሃረነ እና የአሃዱ ሬዴዮና ቴሌቪዥን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጥበቡ በለጠ ናቸው። "የመለያየት አደጋ ያለበት ከዛ እርስ በእርስ የብሄር ግጭት፣ የሃይማኖት ግጭት አፍጦ ባለበት ቦታ ላይ ቀድመህ መቻቻልን ነው የምትሰብከው ግዴላችሁም እንቻቻል፣ አንጣላ፣ ቢያንስ አንዋጋ፣ አንዱ የሌላውን አያቃጥል ብለን ወደ መቻቻል ላይ እናተኩራለን፣ መቻቻል ሲሳካልን ደግሞ ወደ መተሳሰቡ ላይ ደግሞ እናተኩራለለን እሱን ደግሞ ስናልፈው አሁን ደግሞ እንተሳሰብ፣ ፍቅርን እናግንን፣ አንዳችን ለሌላችን እናስብ፣ መልካም ነገር እናድርግ ወደሚለው ደግሞ ይኬዳል፣ ስለዚህ ሁለቱም ያስፈልጉናል እንቻቻላለን ከዛ ደሞ ወደመተሳሰብ እንሄዳለን።" ያሉት  ዶክተር ወዳጄነህ መሃረነ ናቸው፡፡ "መተሳሰብ የበለጠ በጣም ጥሩ ነው ላንተ እኔ ባስብ አንተ ደግሞ ለኔ ብታስብ የበለጠ ጥሩ ነው" ያሉት ደግሞ አቶ ጥበቡ በለጠ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም