ሰላምን ለማረጋገጥ የጸጥታ አካሉ ከህዝቡ ጋር በቅንጅት ሊሰራ ይገባል---የሰቆጣ ነዋሪዎች

70
ሰቆጣ ኢዜአ መስከረም 9 / 2012 - የሰቆጣ ከተማን ሰላም ለማረጋገጥ የጸጥታ አካሉ ከህዝቡ ጋር በቅንጅት ሊሰራ እንደሚገባ ነዋሪዎች አሳሰቡ ። በከተማው ሰላምና ጸጥታ ዙሪያ ነዋሪዎችና የአስተዳደር አካላት የምክክር  መድረክ አካሄደዋል ። በከተማው በሆቴል ስራ የተሰማሩት አቶ ጌጡ ብርሃኑ በሰጡት አስተያየት በነዋሪውና በፀጥታ ኃይሉ መካከል የነበረ ቅንጅታዊ አሰራር በመዳከሙ ሰላምን የሚያውኩ የወንጀል ድርጊቶች እየተበራከቱ መሆናቸውን ተናግረዋል። አስተያየት ሰጪው እንዳሉት ህገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር እየተስፋፋ መምጣቱንና የጸጥታ አካሉ በድርጊቱ መሳተፉ ደግሞ ችግሩን ውስብስብ እያደረገው ነው። የፀጥታ መዋቅሩ ውስጡ ሊፈተሽ እንደሚገባ አመላክተዋል ። ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ  አቶ መኳንት አስፋው በበኩላቸው ለከተማው ሰላም መደፍረስ ምክንያቱ የጸጥታ አካላት ከህዝቡ ጋር ተቀናጅተው ባለመስራታቸው የመጣ ችግር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ስርቆት፣ የድብደባና አግባብነት የሌላቸው የጦር መሳሪያ አጠቃቀም እየተስተዋሉ መሆኑን  ጠቅሰዋል ። “የጸጥታ አካሉና በህብረተሰቡ መካከል ግልፅ ውይይት ባለመደረጉና ግንዛቤ ባለመፈጠሩ የወንጀል ድርጊቶች እየተበራከቱ ነው” ያሉት ደግሞ ሃምሳ አለቃ ሹመት ቸኮለ ናቸው፡፡ ህገወጥ መሳሪያ የታጠቁ ሰዎች መበራከትና  በአግባቡ አለመጠቀም ለሰላም መደፍረሰ ምክንቶች መሆናቸውን አመልክተዋል ። የመቅደላ ብርጌድ ዋና አዛዥ ኮለኔል ሸጋው ጓሌ ህብረተሰቡ በጸጥታ አካሉ ላይ ያነሳቸው የስነ ምግባርና ሌሎች ችግሮች እንዲስተካከሉ እንደሚደረግ ገልጸዋል ። “በህገ ወጥ መሳሪያ ዝውውርና አጠቃቀም ላይ የሚታዩ ችግሮችን መቆጣጠር በጸጥታ አካላት ብቻ የሚሰራ ባለመሆኑ ህብረተሰቡ ህገወጦችን አጋልጦ ሊሰጥና ከጸጥታ አካላት ጋር ተባብሮ ሊሰራ ይገባል” ብለዋል፡፡ የህገ ወጥ መሳሪያ ጉዳይ ለድርድር የሚቀርብ ባለመሆኑ ህግን የማሰከበር ስራ በትኩረት አንደሚሰራ ተናግረዋል ። በከተማዋ  የተሰማሩ የጸጥታ አካላት በተጠናከረ መልኩ ተቀናጅተው የከተማዋን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ እንደሚሰሩ ኮለኔል ሸጋው አስታውቀዋል፡፡ የዋግ ህምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ በሪሁን ኪዳነ ማርያም በበኩላቸው የከተማውንም ሆነ የዞኑን ህዝብ ሰላምና ደህንነት ለማስቀጠል ጠንክረው እንደሚሰሩ ገልጸዋል ። ህብረተሰቡም ጠንካራ ተሳትፎ ሊያደርግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል ። የህብረተሰቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት እየተሰራ ባለበት ወቅት አሉባልታና መሰረት የሌላቸውን መረጃዎች የሚያሰራጩ አካላት ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ እንደሚገባም አሳስበዋል ። በምክክር መድረኩ የጸጥታ አካላት፣  የኃይማኖት መሪዎች፣ የሃገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም