ኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ማበልጸጊያ ማዕከላትን ለመገንባት እየሰራች ነው- የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር

98
መስከረም 9/2012 ኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ከማስፋፋት ጎን ለጎን የቴክኖሎጂ ማበልጸጊያ ማዕከላትን ለመገንባት እየሰራች መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለፀ። ‹‹ተስፋ አይ ኤል ጂ›› በኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ሀሳብ ያላቸውን በተለያየ መልክ ለመደገፍ የሚያስችለውን ስምምነት ከሚኒስቴሩ ጋር ተፈራርሟል፡፡ ስምምነቱን የፈረሙት የኢኖቬሽንና ቴክሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ጀማል በከርና መቀመጫውን ስዊዘርላንድ ያደረገው ‹‹ተስፋ አይ ኤል ጂ›› ድርጅት ፕሬዝዳንት አቶ ዳዊት ተስፋዬ ናቸው። የሚኒስቴሩ የሚዲያና ፕሬስ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ዓለምነው ለኢዜአ እንዳሉት፣ አገሪቷ ቀደም ባሉት ዓመታት የቴክኖሎጂ ማበልጸጊያ ማዕከላትን ያልገነባች በመሆኑ አዳዲስ የፈጠራ ሀሳቦች ተግባር ላይ ሳይውሉ ባክነው ይቀራሉ። በተለይም ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመርቀው የሚወጡ ተማሪዎች ያላቸውን ሀሳብ አበልጽገው ወደ ውጤት እንዲቀይሩት ማዕከላቱ ትልቅ ሚና አላቸውም ብለዋል። የኢንዱስትሪ ፓርኮች ያለ ቴክኖሎጂ ውጤታማ ሊሆኑ አይችሉም ያሉት ዳይሬክተሩ አገሪቷ እየገነባችው ካለው ኢንዱስትሪ ፓርክ ጎን ለጎን የቴክኖሎጂ ማበልጸጊያ ማዕከላትን ለመገንባት እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል። በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ አነሳሽነት በስዊዘርላንድ የተመሰረተው ድርጅቱ አዲስ የቴክኖለጂ ሃሳብ ያላቸው ግለሰቦች ሀሳቦች ተጨባጭ በሆነ መንገድ ወደገበያ ገብተው ተጨባጭ ትርጉም እስኪሰጡ የተለያዩ ድጋፎችን ለማቅረብ ቃል ገብቷል። ከኢኖቬሽንና ቴክሎጂ ሚኒስቴር ጋር የተፈረመው ይህ ስምምነትም የድርጅቱን ዓላማ  ወደተግባር ለመቀየርም የሚያስችል መሆኑን አቶ ተስፋዬ ገልፀዋል። በዚህ ዓመት ወደ ስራ እንደሚገባም አስታውቀዋል። የቴክኖሎጂ ጀማሪዎች የፈጠራ ሃሳቦቻቸውን እንዲያዳብሩ የቴክኖሎጂ ማበልፀጊያ ስልጠና መስጠት፣ ስራዎቻቸው ወደምርት እንዲገቡ የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ፣ የንግድ እቅድ አሰራር ስልጠና እና የቴክኖሎጂ ልምድ ልውውጥ ማድረግ የስምምነቱ አካል ነው፡፡ ስምምነቱ የኢትዮጵያ መንግስት የያዘውን የቴክኖሎጂ ዘርፍ የስራ እድል ፈጠራን የሚያግዝ መሆኑም ነው የተነገረው። የቴክኖሎጂ ማበልጸጊያ ማዕከላቱ አንድ የቴክኖሎጂ  ሀሳብ ዳብሮና በልጽጎ ወደ ናሙና ተቀይሮ ወደ ምርት እንዲሸጋገሩ የሚያግዙ ናቸው።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም