በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለሚገኙ ሴትና አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች የሚውል የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ተካሄደ

180

አዲስ አበባ ኢዜአ መስከረም 9/2012 በመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለሚገኙ ችግረኛ ሴትና አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች የሚውል የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ተካሄደ።

“ለእህቴ” በሚል መጠሪያ ትላንት በብሄራዊ ቤተ መንግስት በተካሄደ መርሃ ግብር ነው ገቢው የተሰበሰበው።

የገቢ ማሰባሰቢያው በፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ሃሳብ አፍላቂነት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገኙ ሴት ተማሪዎችን የኢኮኖሚ ችግር ለማቃለል የተዘረጋ ፕሮጀክት አካል ነው።

ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ በተለያዩ የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገኙ ሴት ተማሪዎች በሚያጋጥሟቸው የኢኮኖሚ ችግሮች ምክንያት ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡና ትምህርታቸውንም ተረጋግተው እንዲከታተሉ የሚያስችላቸውን ድጋፍ ያመቻቻል።

ሴትና አካል ጉዳተኛ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች እያጋጠማቸው ያለውን ችግር በገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሩ ላይ አካፍለዋል።

የትምህርት መሳሪያ ቁሳቁስ፣ የአልባሳት፣ የንጽህና መጠበቂያና ሌሎች እጥረቶች ተማሪዎቹ ከሚያጋጥሟቸው ችግሮች  መካከል መሆናቸውን አንስተው በዚህም ለስነልቦና፣ ትምህርት ማቋረጥና ሌሎች ፈተናዎች ይዳረጋሉ።

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በበኩላቸው ከከፍተኛ ትምህርትና ሳይንስ ሚኒስቴርና ከዩኒቨርስቲ ማህበረሰብ ጋር በተደረገው ውይይት የተጠቀሱት ችግሮች መኖራቸውን ለይተናል ብለዋል።

በመሆኑም በዩኒቨርስቲ የሚገኙ ሴት ተማሪዎች በሚያጋጥማቸው የኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ትምህርት ሳይጨርሱ እንዳያቋርጡ ፕሮጀክት መነደፉን ገልጸዋል።

መርሃ ግብሩ ዩኒቨርስቲዎችን ለሴቶች ምቹና አካታች በማድረግ በኢኮኖሚ ችግር ምክንያት በትምህርታቸው ላይ የሚደርሰውን ጫና ለማቃለል ያለመ መሆኑንም አክለዋል።

የገቢ  ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሩ በጊዜያዊነት ችግርን ለመፍታት ብቻ ተከናውኖ የሚቆም ሳይሆን ተቋማዊ ለማድረግ መሰራት እንዳለበት አሳስበዋል።

እንደፕሬዝዳንቷ ገለጻ የሴቶችን አቅም ለማሳደግ ዩኒቨርስቲዎች ላይ ብቻ ትኩረት ማድረግ ሳይሆን በመካከለኛ የትምህርት ደረጃ የሚገኙ ሴቶችን ክህሎት ለማሳደግም ቋሚ የማሰልጠኛ ማዕከል ለማቋቋም እየተሰራ ነው።

“ከተባበርንና ከተቀናጀን የምንጓዝበትን ርቀትና ፍጥነት ማራዘም እንችላለን” ያሉት ፕሬዝደንቷ 2012 ዓ.ም ቃላችንን ወደተግባር የምንቀይርበት ዓመት መሆን አለበት ሲሉም ጠይቀዋል።

የተሰበሰበው ገቢ በከፍተኛ ትምህርትና ሳይንስ ሚኒስቴር በኩል ለተማሪዎቹ እንዲደርስ ይደረጋል ተብሏል።

በስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኘችው አትሌት ደራርቱ ቱሉ ለኢዜአ በሰጠችው አስተያየየት የሴቶችን ችግር በጋራ ለመፍታት ሁሉም መተባበር እንዳለበት ጠቅሳ እሷም የምታደርገውን ድጋፍ እንደምትቀጥል ቃል ገብታለች።

በገቢ ማሰባሰቢያው ላይ የስዕል ጥበብ ስራዎች ቀርበው የተሸጡ ከመሆኑም በላይ የተለያዩ ተቋማትና ባለሃብቶች ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።

የንግዱ ማህበረሰብና ሌሎች የሚመለከታቸው የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በስነስርአቱ ላይ ተገኝተዋል።