በጌዴኦ ለችግረኛ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ

103

ዲላ ኢዜአ መስከረም 9 ቀን 2012፡- በጌዴኦ ዞን ከ4 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ችግረኛ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን የዞኑ ትምህርት መምሪያ አስታወቀ፡፡

ድጋፉን ያደረጉት  መንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የኃይማኖት ተቋማት፣ እድሮችና ግለሰቦች መሆናቸውን የመምሪያው ኃላፊ አቶ መስፍን ደምሴ ለኢዜአ ገልጸዋል።

ለተማሪዎቹ በድጋፍ የተበረከቱት 40 ሺህ ደብተሮች፣ እስክሪብቶዎችና ሌሎች የትምህርት ቁሳቁሶች ናቸው።

በዞኑ ባለፈው ዓመት ከተመዘገቡ 300ሺህ በላይ ተማሪዎች ውስጥ 10ሺህ የሚሆኑት በትምህርት ቁሳቁስ እጥረት ትምህርታቸውን አቋርጠው እንደነበር አስታውሰው ዘንድሮ የተደረገው ድጋፍ ችግሩን እንደሚያቃልለው ተናግረዋል ።

ድግፉን ካደረጉ ተቋማት መካከል የዲላና አካባቢዋ መተዋወቂያና መረዳጃ ማህበር ተወካይ አቶ ደሙ አብዲ በበኩላቸው ማህበሩ   በ100ሺህ ብር ወጪ ደብተርና እስከሪፕቶ በመግዛት ለ500 ተማሪዎች ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

ችግረኛ ልጆች በትምህርት ቁሳቁስ እጥረት ምክንያት ከትምህርት  ገበታ እንዳይለዩ ማህበሩ የበኩሉን ጥረት ማድረጉን እንደሚቀጥልም አመለክተዋል።

ድጋፍ ከተደረገላቸው  መካከል ተማሪ ብፅዒት መንግስቱ የተደረገላት የደብተረና እሰኪሪብቶ ድጋፍ ትምህርቷን በንቃት እንድትከታተል መነሳሳት የፈጠረላት መሆኑን ገልጻለች።