በከተማዋ እግር ኳስ ደጋፊ ማህበራት ውስጥ የተደራጁ ስራ አጥ ወጣቶች የመስሪያ ቦታ ተሰጣቸው

88
መስከረም 8/2012 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በእግር ኳስ ደጋፊ ማህበራት ውስጥ ለተደራጁ ስራ አጥ ወጣቶች የመስሪያ ቦታ ተሰጠ። የመስሪያ ቦታው  የተመቻቸላቸው የእግር ኳስ ደጋፊ ማህበራት ውስጥ  የተደራጁ በ46 ማህበራት ውስጥ የሚገኙ ከ300 አባላት በላይ ለሚሆኑ ስራ አጥ ወጣቶች ናቸው። ለስራ አጥ ወጣቶቹ የመዲናዋ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በተገኙበት የመስሪያ ቦታው የእጣ አወጣጥ ስነ ስርት ተካሂዳል። የመስሪያ ቦታውን ያመቻቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከወጣቶችና በጎ ፍቃድ ማስተባበሪያ ቢሮና የስራ እድል ፈጠራ ጽህፈት ቤት እንዲሁም ከአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን ጋር በመሆን ነው። ወጣቶቹ የመስሪያ ቦታ የሚውል በኮንዶሚኒየም ቤቶች የሚገኙ የንግድ ሱቆችን የተረከቡ ሲሆን በብረታ ብረትና እንጨት ስራ ላይ እንደሚሰማሩም ተገልጿል። በስነ - ስርዓቱ ላይ የተገኙት ወጣቶች በሰጡት አስተያየት ቀደም ሲል በነበሩት ጊዜያት የአዲስ አበባ ወጣቶች የስራ እድል ተጠቃሚ እንዳልነበሩ ገልጸዋል። በቀጣይ አገር ተረካቢዎች ወጣቶች በመሆናቸው የስራ እድል ተጠቃሚ ሊሆኑ እንደሚገባ ገልጸው፤ ይህንን ላደረጉ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል። ''ወጣቶቹ ውጤታማ እንዲሆኑ በየደረጃው ያሉ ቢሮዎች ውስጥ የሚያጋጥማቸው የመልካም አስተዳደር ችግር ሊፈቱ ይገባል'' ብለዋል። በግላቸው የተደራጁት ማህበራትም ወቅቱን ያገናዘበ የፋይናንስ ብድር እንዲሰጣቸው ጠይቀው ሌሎች በመዲናዋ የሚኖሩ ስራ አጥ ወጣቶችም የስራ እድል እንደተመቻቸላቸው ጠይቀዋል። እንዲሁም ለስራ አጥ ወጣቶች የመስሪያ ቦታ እድል ማመቻቸት የሚያበረታታ መሆኑን የገለጹት ወጣቶቹ፤ በቀጣይ የክትትልና ድጋፍ ስራው ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀዋል። ወጣቶቹ  ላነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ የመዲበናዋን ወጣቶች በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። በመሆኑም በዚህ ዓመት በመዲናዋ ከ250 ሺህ በላይ ስራ አጥ ወጣቶችን ወደ ስራ ለማስገባት እቅድ መያዙን ጠቁመዋል። ወጣቶቹ በሚሰማሩበት ስራ ውጤታማ እንዲሆኑም ክትትልና ድጋፍ እንደሚደረግም አረጋግጠዋል። የመዲናዋን ልማት ለማሳደግና ወጣቶቹ ለውጤታማነት ይበቁ ዘንድ በትዕግስት ህጋዊ ያልሆኑ አሰራሮችን ለማረም እንዲታገሉ ጠይቀዋል። በአብዛኛው የመስሪያ ቦታው የተበረከተላቸው የቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ደጋፊ ማህበራት ውስጥ ያሉ ወጣቶች ናቸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም