ከባህርዳር ጭስ አባይ ኮንክሪት አስፓልት መንገድ ግንባታ ተጀመረ

መስከረም 8/2012 ከባህርዳር ጭስ አባይ የሚወስደውን መንገድ በኮንክሪት አስፓልት ደረጃ ለማስገንባት በ767 ሚሊየን ብር የማስጀመሪያ ፕሮግራም ስራ ዛሬ ተካሂዷል። በመንገድ የማስጀመሪያ ስነ-ስርዓቱ ላይ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮነን የሚመራ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት ማምሻውን ሰባታሚት በሚባለው ቦታ ተገኝተዋል። 22 ኪሎ ሜትር ርዝመትና 30 ሜትር ስፋት ያለው የኮንክሪት አስፓልት መንገድ ግንባታ በሁለት ዓመት ተኩል ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል። ሜልኮል በተባለ አገር በቀል የስራ ተቋራጭ የሚገነባው መንገድ የጤስ አባይ ፏፏቴን ለመጎብኘት ለሚመጡ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ጎብኚዎች ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ተብሏል። የመንገድ ግንባታው የዲዛይን ስራ በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል። በጢስ አባይ አካባቢ በስፋት እየለማ የሚገኘውን የሸንኮራ አገዳና ሌሎች የግብርና ምርቶች በቀላሉ አጓጉዞ ለከተማው ማህበረሰብና ለኢንዱስትሪ ለማቅረብ ጠቃሜታው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል። መንገዱ እድገቷ ተወስኖ የኖረውን የጢስ አባይ ከተማ እድገት ከማፋጠኑም በተጨማሪም ለአካባቢው ስራ አጥ ወጣቶች የስራ እድል የሚፈጥር ነው ተብሏል። በስነ-ስርዓቱ ላይም አቶ ደመቀ መኮንንን ጨምሮ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህና ሌሎች የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም