ለሁሉም ክፍት በሆነው የወርልድ ቴኳንዶ ዛሬ የፍጻሜ ውድድሮች ተካሄደዋል

154

መስከረም 8/2012 ለሁሉም ክፍት በሆነው የወርልድ ቴኳንዶ ዛሬ የመጀመሪያ የፍጻሜ ውድድሮች ተካሄደዋል።
የወርልድ ቴኳንዶ ውድድሩ ትናንት ቦሌ በሚገኘው የብሔራዊ ስፖርት ፌዴሬሽኖች ጅምናዚየም መጀመሩ ይታወሳል።

በውድድሩም ከዘጠኙ ክልሎችና ከሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ከ150 በላይ ተወዳዳሪዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

በሴት ከ49፣ 57 እና 67 ኪሎ ግራም በታች እንዲሁም በወንድ ከ58፣ 60 እና 80 ኪሎ ግራም በታች ውድድሩ የሚካሄድባቸው የክብደት ዘርፎች ናቸው።

ትናንት በመጀመሪያ ቀን በሴት ከ57 እና ከ67 ኪሎ ግራም በታች እንዲሁም ከ68 ኪሎ ግራም በታች ወንድ የፍጻሜ ውድድሮች እንደሚካሄዱ የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ገልጾ ነበር።

ነገር ግን የማጣሪያ ጨዋታዎች ቁጥር በመብዛቱ  ምክንያት የፍጻሜ ጨዋታዎቹን በተባለው ቀን ማካሄድ ባለመቻሉ ጨዋታዎቹ አድረው ዛሬ ተደርገዋል።

በዚሁ መሰረት ከ57 ኪሎ ግራም በታች ሴት የአማራ ክልል ተወዳዳሪዋ መቅደስ አዝመራው ሌላኛዋን የአማራ ክልል ተወዳዳሪ ምህረት ሞላን በማሸነፍ የወርቅ ሜዳሊያ ስታገኝ ምህረት የብር ሜዳሊያ አግኝታለች።

የኦሮሚያ ክልል ተወዳዳሪ የሆኑት አሚን ሚኤሶና አያንቱ ሚኤሶ በዚሁ የክብደት ዘርፍ የነሐስ ሜዳሊያ ማግኘት ችለዋል።

ከ67 ኪሎ ግራም በታች ሴት የደቡብ ክልሏ ተወዳዳሪ አይኔ አሰፋ የኦሮሚያዋን መስከረም ሽፈራውን በማሸነፍ የወርቅ ሜዳሊያ ስታገኝ መስከረም የብር ሜዳሊያ ባለቤት መሆን ችላለች።

የአማራ ክልል ተወዳዳሪ የሆነችው ረድኤት ጌታቸው እና የኦሮሚያ ክልል ተወዳዳሪዋ ወርቄ ሚልኬሳ በዚሁ የክብደት ዘርፍ የነሐስ ሜዳሊያ አግኝተዋል።

ከ68 ኪሎ ግራም በታች ወንድ የኦሮሚያ ክልሉ ጀማል ሀጂ የአዲስ አበባውን ገመቺስ ኤፍሬም በማሸነፍ የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘ ሲሆን ገመቺስ የብር ሜዳሊያ አግኝቷል።

የአዲስ አበባው አብዱልፈታ ሰፋና የኦሮሚያው ዮሐንስ ለማ የነሐስ ሜዳሊያ ያገኙ ተወዳዳሪዎች ናቸው።

ዛሬ ከ58 እና ከ80 ኪሎ ግራም ወንድ ከ49ኪሎ ግራም ሴት የፍጻሜ ውድድሮች እንደሚካሄዱ መርሃ ግብር የወጣ ሲሆን በአሁኑ ሰአት  በብሔራዊ ስፖርት ፌዴሬሽኖች ጅምናዚየም የውድድሮቹ የማጣሪያ ጨዋታዎች እየተካሄዱ ይገኛሉ።

ለሁሉም ክፍት የሆነው የወርልድ ቴኳንዶ ውድድር ነገ ፍጻሜውን ያገኛል።

እ.አ.አ በ2020 በቶኪዮ ለሚካሄደው የኦሊምፒክ ውድድር በጥር ወር 2012 ዓ.ም በሞሮኮ በሚካሄደው የማጣሪያ ውድድር ነባሩን የወርልድ ቴኳንዶ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ የሚካተቱ ስፖርተኞችን መምረጥ የውድድሩ ዋንኛ አላማ እንደሆነ ተገልጿል።

ለተወዳዳሪዎች የውድድር አማራጭ መፍጠርና አቋማቸውን እንዲለኩ ማድረግም ውድድሩ የተዘጋጀበት ሌላኛው አላማ ነው።