በወልቂጤ ከተማ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ አጠቃላይ ሆስፒታል ሊገነባ ነው

96
ሀዋሳ ኢዜአ መስከረም 08/2012፡- በወልቂጤ ከተማ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ አጠቃላይ ሆስፒታል ለመገንባት ዛሬ የውል ስምምነት ተፈረመ። የውል ስምምነቱ የተፈራረሙት የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ እና  ግንባታውን የሚከናውነው ተቋራጭ ናቸው። የቢሮው ኃላፊ አቶ አቅናው ካውዛ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት ከዚህ በፊት የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ይገነቡና በደረጃ እያሳደጉ ሲሄዱ ቆይተዋል። በወልቂጤ ከተማ የሚገነባው አጠቃላይ ሆስፒታል በክልሉ የመጀመሪያውና 594 ሚሊዮን ብር የሆነው ወጪው በክልሉ መንግስት የሚሸፈን መሆኑን አመልክተዋል። የሆስፒታሉ ግንባታ በአካባቢው ለረጅም ጊዜ የቆየ የመልካም አስተዳደር ችግር እንደነበረም አውስተዋል ፡፡ ሆስፒታሉ በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ተጠናቆ ለህዝቡ አገልግሎት እንዲውል በየደረጃው ያሉ ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንደሚያሻ አመልክተዋል ፡፡ የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ጀማል በበኩላቸው በወልቂጤ ከተማ ከዚህ በፊት ሊገነባ የመሠረት ድንጋይ ተቀምጦ ሳይካሄድ የቀረው ሆስፒታል በህዝቡ ዘንድ ቅሬታ ፈጥሮ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡ የክልሉ መንግስት ምላሽ ለመስጠት ቃል በገባው መሰረት በምትኩ ይህንን ሆስፒታል ለመገንባት መወሰኑ ቁርጠኝነቱን እንደሚያሳይ ተናግረዋል ፡፡ አጠቃላይ ሆስፒታሉ በወቅቱ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃም ከህዝቡ ጋር በትብብር እንደሚሰሩ አስታውቀዋል ፡፡ የክልሉ መንግስት የህዘቡን ጥያቄ ለመመለስ የሄደበትን ርቀትም አድንቀዋል ፡፡ ግንባታውን የሚያከናውነው ተቋራጭ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮሐንስ ኃይሌ በሆስፒታል ግንባታ ሰፊ ልምድ እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡ አጠቃላይ ሆስፒታሉ በተያዘለት ጊዜ ገደብ ውስጥ እንዲጠናቀቅ ያላሰለሰ ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል ፡፡ እንደ አቶ ዮሐንስ ገለፃ የሆስፒታሉን ግንባታ ለማጠናቀቅ የ900 ቀናት የጊዜ ገደብ ተቀምጦለታል ፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም