በአዲስ አበባ ከተማ ዋጋ በማናር 609 ድርጅቶችና የንግድ ሱቆች መታሸጋቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ ኢዜአ መስከረም 8/2012 በአዲስ አበባ ከተማ የዋጋ ንረትን በመጨመር የኑሮ ውድነትን አባብሰዋል የተባሉ 609 ድርጅቶችና የንግድ ሱቆች መታሸጋቸውን የአስተዳደሩ ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ አስታወቀ። ህግን ከማስከበር ባለፈ ህገወጥ ንግድን ለመከላከል የሚያስችሉ ዘላቂ መፍትሄዎችን ለመስጠት ቢሮው እየሰራ መሆኑንም ገልጿል። የአዲስ አበባ የንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ በመዲናዋ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ንረትና የሚያስከትለውን የኑሮ ውድነት በሚመለከት እየወሰደ ያለውን የማስተካከያ እርምጃ አስመልክቶ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል። የቢሮው ሃላፊና በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ ኢንጂነር እንዳወቅ አብጤ በአዲስ አበባ ያለውን የዋጋ ንረትና ኑሮ ውድነት በተያያዘ ቀጥታ ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ባላቸው ድርጅቶችና የንግድ ሱቆች ላይ ፍተሻ መደረጉን ገልጸዋል። በእህልና ጥራጥሬ፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ በቁም እንስሳት ውጤቶች፣ በግንባታ ግብአቶችና መጋዘኖች ላይ ዋነኛ ትኩረት ተደርጎ የኑሮ ውድነት በከፍተኛ ሁኔታ ከተባባሰበት ከግንቦት ወር 2011 ዓ.ም ጀምሮ ህግና ስርአትን የማስከበር ስራ እየተሰራ መቆየቱን አመልክተዋል። በዚህም መሰረት በንግድ ሱቆችና ድርጅቶች ላይ በተደረገው ፍተሻና ክትትል በከተማዋ የዋጋ ንረትን በመጨመር የኑሮ ውድነትን አባብሰዋል የተባሉ 609 ድርጅቶችና የንግድ ሱቆች መታሸጋቸውንና ከ2 ሺህ 300 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው ገልጸዋል። 93 ዳቦ ቤቶች፣ 91 ወፍጮ ቤቶች፣ 63 ስጋ ቤቶች፣ 56 አትክልት እና ፍራፍሬ ቤቶች፣ 55 የኮንስትራክሽን እቃ መሸጫዎች፣ 53 እህል ቤቶችና 28 ምግብ ቤቶች ከታሸጉት መካከል እንደሚገኙበትም ገልጸዋል። መጋዘኖች፣ ሌሎች ማከማቻዎች፣ የችርቻሮ ሱቆችና ሌሎች ዘርፎች የሚገኙ ተቋማትም መታሸጋቸውን፤ ህገወጥ ድርጊት የፈጸሙት ድርጅቶችና የንግድ ሱቆችና ድርጅቶች አስተዳዳራዊና የህግ እርምጃዎች እንደሚወሰድባቸው አመልክተዋል። ባለፉት ሁለት ሳምንታት በአትክልት ተራ ህገ ወጥ ንግድና ህገ ወጥ ነጋዴዎችን ለመቆጣጣር በተከናወነ ስራ በ59 መኪኖች ላይ የሚገኙ የአትክልትና የፍራፍሬ ምርቶች መያዛቸውንና ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲደርስ መደረጉን ገልጸዋል። ቢሮው ከአስተዳደሩ ገቢዎች ባለስልጣን፣ ዐቃቤ ሕግ ቢሮ፣ የሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮና ፖሊስ ኮሚሽን ጋር ተቀናጅቶ በመስራት የቁጥጥርና የህግ ማስከበር እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን ጠቁመዋል። ህግ የማስከበር ተግባሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና በቀጣይ ለህብረተሰቡ ይፋ እንደሚደረግ ኢንጂነር እንዳወቅ ተናግረዋል። በግብይት ሰንሰለት ውስጥ እሴት የማይጨምሩ የኑሮ ውድነትን እያባበሱ ያሉት ህገ ወጥ ደላሎችን ከሰንሰለቱ በመቁረጥ አምራችና አቅራቢ እንዲገናኙ የሚያስችሉ ስራዎች እንደሚከናወኑም ተናግረዋል። ''ባለፉት ጥቂት ወራት መሰረታዊ በሚባሉ ሸቀጦች ላይ የሚታየውን የአቅርቦት ችግር ለመፍታት ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው'' ብለዋል። በዚሁ መሰረት በአዲስ አበባ ከተማ በየወሩ 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሊትር ዘይት፣ 120 ሺህ ኩንታል ስኳር እና 165 ሺህ 657 ኩንታል ስንዴ እየቀረበ መሆኑንና የአቅርቦት ችግሩ እየተቃለለ መምጣቱን ጠቅሰዋል። ከህግ ማስከበሩ ባለፈ የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የመንግስት ልማት ድርጅቶችና የህብረት ስራ ማህበራት በምርት ስርጭት ውስጥ ገብተው ገበያውን የማረጋጋት ስራ እንዲሰሩ እንደሚደረግ ገልጸዋል። ህብረተሰቡ የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት እያባባሱ የሚገኙትን ህገ ወጥ አካላት በመጠቆም አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግም ጠይቀዋል። በአዲስ አበባ ፈቃድ የተሰጣቸው 372 ሺህ የንግድ ድርጅቶች እንደሚገኙ ከአዲስ አበባ ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም