በሀዋሳ ኮሌራ እንዳይስፋፋ የቁጥጥር ሰራ እየተካሄደ ነው

67

መስከረም 8/2012 በሀዋሳ ከተማ ኮሌራ በሽታ ስርጭት እንዳይስፋፋ የቁጥጥር ሰራ እየተካሄደ መሆኑን የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ።

በቢሮው የጤናና ጤና ነክ ድንገተኛ አደጋዎች ቅኝትና ምላሽ ዋና የስስራ ሂደት ባለቤት አቶ እንዳሻው ሽብሩ ለኢዜአ እንደገለጹት በከተማው በቅርቡ በተከሰተ የኮሌራ የተያዙ 92 ሰዎች በጤና ተቋማት የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርጓል ።

በማእከላት ተኝተው የህክምና አገልግሎት ካገኙት ውስጥ 86ቱ ድነው ወደ ቤታቸው መመለሳቸውን ተናግረዋል።

ቀሪዎቹ ስድስት ህሙማን ህክምናውን በመከታተል ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል ።

“የበሽታው ስርጭት በክልሉ ከሚገኙ ዞኖች፣ ልዩ ወረዳዎችና አጎራባች የኦሮሚያ ዞኖች ጋር በጋራ እየተሰራ ነው” ብለዋል።

በሽታው ከመፀዳጃ አጠቃቀምና ከመጠጥ ውሀ ንፅህና ጉድለት ጋር ተያይዞ  እንዳይሰፋፋ የውሀ ማከሚያ ኬሚካል ስርጭትና የግንዛቤ  የማስጨበጥ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል ።

በሽታው በንጽህና ጉድለት ምክንያት በፍጥነት ሊዛመት ስለሚችል ከትምህርት ከውሃና ግብርና ቢሮዎች እንዲሁም ከዕምነት ተቋማት ጋር በመቀናጀት የቁጥጥር ሰራው እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ትምህርት መጀመሩን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ተማሪዎችን በትምህርት ቤቶቻቸው ስለበሽታው የማስተማርና ቤተሰቦቻቸውን የማሳወቅ  ስራ እንደሚሰራ አመላክተዋል ።

ህብረተሰቡ ያልበሰሉ ምግቦችን ከመመገብና ንጽህናው ያልተጠበቀ ውሃን ባለመጠቀም ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባው  የገለፁት  አቶ እንዳሻው  በተለይ  በሀዋሳ ሀይቅ አካባቢ በጥሬ የሚበሉ ምግቦች ላይ ህብረተሰቡ እንዲጠነቀቅ አሳስበዋል።

በአዳሬ ጤና ጣቢያ የኮሌራ ህሙማን ማከሚያ ጊዜያዊ ማዕከል አስተባበሪ አቶ ተስፋዬ አለሙ በበኩላቸው በበሽታው ተይዘው ወደ ማዕከሉ የመጡ ከ70 በላይ ሰዎች ህክምና ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

በማዕከሉ በየቀኑ የሚመጡ ህሙማን እንዳሉና ምርመራ ተደርጎ ኮሌራ ሆኖ ከተገኘ ለብቻ ሆነው ህክምና እንደሚደረግላቸ ጠቅሰዋል ።

በተጨማሪም ወደ መኖሪያ ቤታቸው በመሄድ የኬሚካል ርጭትና የግንዛቤ ማጎልበቻ ስልጠና እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

በማዕከሉ የጤና ባለሙያ የሆነው ነርስ ደሞዜ አሰፋ “በከተማው ከተለያዩ አካባቢዎች ለህክምና የሚመጡትን በመቀበል ህክምና እንዲያገኙ እየተደረገ ነው” ብሏል ።

የተወሳሰበ የጤና ችግር ያለባቸው ህሙማን ሲያጋጥሙ ለከፍተኛ ህክምና ወደ ሀዋሳ ኮምፕሬንሲቭ ሆስፒታል እደሚላኩ ገልጿል ።

እንደ ነርስ ደሞዜ ገለጻ እስካሁን በኮሌራ በሽታ ምክንያት በማዕከሉ የሞተ የለም ።

በክልሉ ጤና ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ቀድራላ አህመድ ስለበሽታው ምንነት መተላለፊያና መከላከያ መንገዶቹ ዙሪያ ግንዛቤ የማሳደግ ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል ።

በሽታው ይከሰትባቸዋል ተብሎ በሚጠረጠሩ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር የመከላከል ስራ ለመስራት እንቅስቃሴ መጀመሩን አቶ ቀድራላ  አስታውቀዋል ።