ወጣቶች ስራን ባህል በማድረግና ጥራትና ብዛት ያላቸው ምርቶች ሊያመርቱ ይገባል--የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር

53
መስከረም 8/2012 ሃገራችን ተወዳደሪ የሆኑ የጋርመንትና የጨርቃጨርቅ ምርቶች ለዓለም ገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆን የሚቻለው ለስራና ጥራት ትኩረት የሚሰጥ ዜጋ ማፍራት ሲቻል መሆኑን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ገለጹ። አውሮፓ ህብረት ባደረገው የገንዘብ ድጋፍ በመቀሌ ለሚገኝ  የጋርመንትና ጨርቃ ጨርቅ ማሰልጠኛ ማእከል የተደረገ የውስጥ ማሽነሪ የሟሟያ ስራ ተጠናቆ ዛሬ ተመርቋል። በማእከሉ ምረቃ የተገኙት የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ወይዘሮ ፈትለወቅር እንዳሉት  ''ወጣቱ ትውልድ በስራው ታታሪና ለምርት ጥራት መጠበቅ ትኩረት መስጠት አለበት'' ብለዋል። በመቐለ የተከፈተው ጋርመንትና ጨርቃ ጨርቅ ማሰልጠኛ ማእከል እንደ እድል በመጠቀም በዘርፉ ፈጣን እድገት ለማምጣት መትጋት እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል፡፡ ብዛትና ጥራት ያለው ምርት ለማቅረብም በትጋት የሚሰራ ዜጋ ለመፍጠር በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ገልጸዋል። ወጣቶች ከመሰደድ በሃገራችው ልማት በሰላም እየሰሩ ራሳቸውን ተጠቃሚ በማድረግ የሃገራቸውን ልማት እንዲያፋጥኑ የጠየቁት ደግሞ የኢትዮጵያ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዳስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ለማ ናቸው። የመቐለ ጋርመንት ዲን አቶ ጌታሁን ለገሰ በበኩላቸው የጋርመንትና ጨርቃ ጨርቅ ማእከል ባሉት 140 የስፌትና ቅድ ማሸነሪዎቹ አማካኝነት ወጣቶች ተቀብሎ ማሰልጠን መጀመሩን ገልጸዋል። ማሺነሪዎቹ የአውሮፓ ህብረት በጣልያን የልማት ትብብር ድርጅት አማካይነት በሰጠው በ100 ሺህ ዩሮ  ድጋፍ የተተከሉ መሆናቸውን ዲኑ ገልጸዋል። ማእከሉ በየወሩ  ከ200 በላይ ወጣት ሰልጣኞች የመቀበል አቅም እንዳለው የገለፁት አቶ ጌታሁን በዚሁ ማእከል ለአንድ ወር ያህል  በቅድና ስፌት ሞያ  የሰለጠኑ196 ወጣቶች በእለቱ መመረቃቸውን ተናግረዋል፡፡ የማእከሉ ህንጻ የከልሉ መንግስት በ10 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ ያዘጋጀው መሆኑን ይታወቃል። ለማእከሉ ማሽነሪዎች ሟሟያ ድጋፍ ያደረገው የጣልያን የልማት ትብብር ድርጅት ተወካይ ሚስስ Aurelia calabro በበኩላቸው እንዳሉት ድጋፉ የተደረገው በህገወጥ ስደት ምክንያት ለአደጋ የሚጋለጡ ወጣቶች በሃገራቸው ሰርተው እንዲለወጡ ከማሰብ መሆኑን ተናግረዋል። ስልጠና ከወሰዱት ወጣት ተመራቂዎች መካከል  ወጣት መዲና ህጉስ ከዚህ በፊት የአስረኛ ክፍል ትምህርት አጠናቃ ውጤት ስላልመጣላት የቤተሰብ ጥገኛ ሆና መቆየቷን ገልፃለች። አሁን የእድሉ ተጠቃሚ በመሆኗ  ሰርታ ለማደግ ፍላጎቷ ከፍተኛ መሆኑን ተናግራለች፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም