ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋን ለማሻሻል ይፋ ላደረገችው መረሐ ግብር ቻይና ድጋፍ እንደምታደርግ ገለጸች

126

መስከረም 8/2012 ኢትዮጵያ ድህነትን ለመቀነስና ኢኮኖሚዋን ለማሻሻል ይፋ ያደረገችውን አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መረሐ ግብር እውን እንዲሆን የቻይና መንግሥትና ሕዝብ እንደሚደግፉት በኢትዮጵያ የቻይና መንግሥት ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር አስታወቁ።

ድህነትን ለመቀነስ የሚሰራው ‘ቻይና ፋውንዴሽን ፎር ፖቨርቲ አሊቬሽን’ በኢትዮጵያ ቅርንጫፉን ከፍቷል።

‘ቻይና ፋውንዴሽን ፎር ፖቨርቲ አሊቬሽን’ በመባል የሚታወቀው ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅት የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ቢሮ መክፈቱን የተመለከተ መርሃ ግብር ተካሂዷል።

አምባሳደር ታን ጃያን በመርሃ ግብሩ ላይ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ በተጠናቀቀው የሚሌኒየም የልማት ግብ ድህነትን ከ39 ከመቶ ወደ 24 ከመቶ በመቀነስ ለዓለም ሕዝብ አርአያነቷን አስመስክራለች።

የዘላቂ ልማት ግብን ለማሳካት የምታደርገውን ጥረትና በቅርቡ ይፋ ያደረገችውን የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ ግብር የቻይና መንግሥትና ሕዝብ ለማገዝ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያና ቻይና የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩበትን 50ኛ ዓመት ጥቅምት 20 ቀን 2012 ዓ.ም ለማክበር በዝግጅት ላይ እንደሚገኙ አምባሳደሩ ጠቁመዋል።

የቻይና መንግሥት ባለፉት 50 ዓመታት ከመሠረተ ልማት ግንባታና ከኢንቨስትመንት ትብብር በተጨማሪ በርካታ የሰብዓዊ ልማት ድጋፎችን ለኢትዮጵያ ማድረጉን አስረድተዋል።

በሰብዓዊ ልማት ድጋፍ ከአራት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ተከስቶ በነበረው የአየር መዛባት ለተጎዱ ወገኖች 60 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት የምግብ እርዳታ ድጋፍ መሰጠቱን ያስታወሱት አምባሳደሩ ፤ በግብርና፣ በትምህርትና በጤና ዘርፍ የሙያና የቴክኒክ ድጋፍ የሚያደርጉ በርካታ ቻይናዊያን በኢትዮጵያ መኖራቸውን ገልጸዋል።

”ዛሬም በይፋ ቢሮ በኢትዮጵያ መክፈቱን የምናበስረው ቻይና ፋውንዴሽን ፎር ፖቨርቲ አሊቬሽን በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ልማት እርዳታን አጠናክረን ለመቀጠል ቁርጠኝነት እንዳለን ያሳያል” ብለዋል።

በፋውንዴሽኑ የኢትዮጵያ ምክትል ዳይሬክተር ዋንግ በበኩላቸው ፋውንዴሽኑ በኢትዮጵያ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ከተለያዩ አጋሮች ጋር በመተባበር የሰብዓዊ ልማት ሲያከናውን መቆየቱን ገልጸዋል።

ፋውንዴሽኑ ባለፉት አራት ዓመታት በኢትዮጵያ ከሚሠሩ አገር በቀልና ዓለም አቀፍ ግብረሰናይ ድርጅቶች ጋር በመተባባር በትምህርት ቤት ምገባ፣ በንጹህ ውሃ አቅርቦትና በሴቶች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ላይ በ74 ሚሊዮን ብር ወጪ 27 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያንን ተጠቃሚ ማድረጉን ተናግረዋል።

ፋውንዴሽኑ በቅርቡ ከኢትዮጵያ የበጎ አድራጎት ማኅበራት ኤጀንሲ ፈቃድ በማግኘቱ ቢሮውን በኢትዮጵያ በይፋ መክፈቱን ኃላፊው አብስረዋል።

‘ቻይና ፋውንዴሽን ፎር ፖቨርቲ አሊቬሽን’ በቀጣይ የዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት ኢትዮጵያ በትምህርት፣ በንጹህ መጠጥ ውሃና ሃይጅን፣ በኢኮኖሚ ዕድገትያስቀመጠችውን ግብ ዕውን እንዲሆኑ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሠሩ ምክትል ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።

ፋውንዴሽኑ ቢሮውን በኢትዮጵያ መከፈቱን ይፋ ባደረገበት ወቅት ‘ፓንዳ ፓክ’ ብሎ በሰየመው ግብረ ሰናይ መርሐ ግብር 43 ሺሕ የደብተር ቦርሳዎች ከነ ቁሳቁሶቹ ለተለያዩ አገር በቀል ግብረ ሰናይ ድርጅቶች አስረክቧል።

በኢትዮጵያ ባለፉት አራት ዓመታት ከተለያዩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር በትብብር ሲሠራ የቆየው ፋውንዴሽኑ ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅት ባለፉት 30 ዓመታት ኢትዮጵያን ጨምሮ በ20 በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ላይ የግብረ ሰናይ ሥራዎችን ሲሠራ መቆየቱም ተመልክቷል።