በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን እስካሁን 81 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር ተሸፈነ

ነገሌ ኢዜአ መስከረም 8/2012 በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን 81 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈኑን የዞኑ ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡ በጽህፈት ቤቱ የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ዘውዴ በቀለ እንዳሉት በጉጂ ዞን ከሀምሌ እስከ ጥቅም 30 የመኸር አዝመራ የዘር ወቅት ነው፡፡ በዚሁ ወቅትም 160 ሺህ 450 ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን 3 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን ገለፀዋል፡፡ እስካሁን 81 ሺህ ሄክታር መሬት ገብስ፣ ባቄላ፣ ስንዴ፣ ጤፍና በቆሎን ጨምሮ በተለያዩ ሰብሎች በዘር እንደተሸፈነ ጠቁመዋል፡፡ በዞኑ የመኼር አዝመራ እየተሳተፉ ካሉ 61 ሺህ 200 አርሶ አደሮች መካከል 4 ሺህ የሚሆኑት ሴቶች እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡ በዘንድሮው የመኸር ወቅት በተለያየ ዘር ለመሸፈን የታቀደው መሬት መጠን ካለፈው አመት በ7 ሺህ ሄክታር የሚጠበቀው ምርት ደግሞ በ126 ሺ ኩንታል እንደሚበልጥ ይጠበቃል ብለዋል፡፡ የመኸር አዝመራውን ምርት ለማሳደግ ከቀረበው 69 ሺ 500 ኩንታል የምርት ማሳደጊያ ውስጥ እስካሁን ግማሽ ያህሉ ጥቅም ላይ መዋሉን ጠቁመዋል፡፡ የዝናቡና የአዝመራው ወቅት እየተገባደደ በመሆኑ አርሶ አደሩ በፍጥነት ቀረውን ማሳ በዘር እንዲሸፍን ባለሙያው ምክር ሰጥተዋል፡፡ በዞኑ አናሶራ ወረዳ የራያ ቦዳ ቀበሌ አርሶ አደር ገመዳ ሶራ ማደበሪያ በወቅቱ በመቅረቡ አብዘኛውን የዘር ስራ እንዳጠናቀቁ ገልጸዋል፡፡ ከ10 ሄክታር መሬት 160 ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ያቀዱትን ለማሳካት ጸረ አረምና ተባይ መከላከያ መድሀኒት እንዲቀርብ ጠይቀዋል፡፡ የዚሁ ወረዳ አርሶ አደር እያሱ ሾንቃ የዘር ስራቸውን ፈጥነው ለማጠናቀቅ በደቦ ባህላዊ የአሰራር ስርአት እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ካዘጋጁት 8 ሄክታር መሬት ሰባቱን በዘር እንደሸፈኑት የገለጹት አርሶ አደሩ የጸረ ተባይ መድሀኒት አቅርቦት ከወዲሁ ሊቀርብላቸው እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም