አዲሱ የኢኮኖሚ ማሻሻያና የመፍትሄ እርምጃዎች

92

የኢትዮጵያ መንግስት ጵጉሜ ሶስት ይፋ ያደረገው” ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም” የውጭ ምንዛሪ ክምችትን ለማሳደግና ለውጭ ባለሃብቶች ምቹ ከባቢ ሁኔታን ለመፍጠር ያለመ ነው።

በአገሪቱ ለኢንቨስተሮች የሚደረገውን ጥበቃና እገዛ ማጠናከር፤እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ ክምችቱን የማሳደግ ግቡ እኤአ በ2020 እስከ 2021 ሊሳካ እንደሚችል በአይ ኤች ኤስ ማርኬት የሰሃራ በታች አገራት ከፍተኛ የኢኮኖሚ ተንታኝ የሆኑት አሊሳ ስትሮቤልና ክሪስ ሳክሊንግ ይፋ ባደረጉትና አይ ኤች ኤስ ማርኬት ድረገጽ ላይ በሰፈረው ሳይንሳዊ ትንተና አመላክተዋል።

በ2019 የአገሪቷ አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት እድገት 7 ነጥብ 7 ሊሆን እንደሚችል በመተንበይ የኢኮኖሚ ሽግግሩን ከመንግስትና ከውጭ የእዳ ፋይናንስ በማላቀቅ ተቀማጭ ሃብትን (equity-based) መሰረት ወደ አደረገ ኢንቨስትመንት ለማሸጋገር በመንግስት ስር ያሉትን ግዙፍ ተቋማት ወደ ግል ይዞታ ለማዞር ጥረት ተጀምሯል ብሏል።

አዲስ የተዋቀረው ብሄራዊ የማሻሻያ ኮሚቴ የኢኮኖሚ እድገቱን ቀጣይነትና የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰቱን ያሳድጋሉ ያላቸውን የተለያዩ እርምጃዎች እየወሰደ ይገኛል።

በተለይ በመንግስት ይዞታ ስር የሚገኙትን ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችና የፖሊሲ ማሻሻያዎች በማድረግ እኤአ በ2020 ምህዳሩን ለማስፋት እየሰራ ነው።

በአዲሱ ኮሚቴ ውስጥ ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ የጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮ፣ ብሄራዊ ባንክና ንግድ ባንክ ተካተውበታል።

በአጠቃላይ የኮሚቴው ተልዕኮም ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት እንዲኖር ማስቻል ነው።

ኮሚቴው የለያቸውንና ፈጣን መፍትሄ ያስፈልጋቸዋል ያላቸውን ጉዳዮች ቢያስቀመጥም የተለየ የፖሊሲ ማዕቀፍ አለመቀመጡን ተመራማሪዎቹ ጠቅሰዋል።

የኢኮኖሚ ማሻሻያው በሚያዚያ 2010  ዓ.ም “አዲስ የተስፋ አድማስ “ በሚል በዶክተር አብይ አህመድ በአገሪቱ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ ሲተገበር ቢቆይም ኮሚቴው  ግን ኢኮኖሚውን በተለየ መንገድ ማሳደግ እንዳለበት አቅጣጫ ተቀምጦለታል።

የውጭ ምንዛሪ እጥረት የውጭ ባላሃብቶች በስፋት ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገቡ እንቅፋት መሆኑ ይታወቃል።

ይህም በተለይ ከግብርና ውጭ ያሉትን የግንባታ፣ የማምረቻና የቱሪዝም ዘርፉን እድገት ገድቦ ይዞታል።

በአገሪቷ ያለው የውጭ ምንዛሪ ክምችትም ያን ያህል የሚያኩራራ አለመሆኑን ባለሙያዎቹ ጠቅሰውታል።

የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ መገለጫ ከሆኑት መካከል ከግብርና ውጭ ያለው የወጪ ንግድ በሚፈለገው ልክ አለማደግ ይጠቀሳል።

እኤአ በ2018/19 የመጨረሻዎቹ ሶስት ወራት አጠቃላይ የወጪ ንግዱ እድገት ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ7 በመቶ ቀንሷል።

አገራዊ ጥቅል እድገቱ በአብዛኛው በመንግሰት ካፒታል በሚከናወኑ ኢንቨስትመንቶች ላይ የተመሰረተና ከወጪ ንግድ አፈጻጸም ጋር ትስስር የሌለው ነው።

በሰኔ 2019 የተመዘገበው የወጪ ንግድ 678 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን ወደ አገር ወስጥ የገባው እቃ ደግሞ 3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ አለው።

በመሆኑም ኮሚቴው ይህንን የገቢና ወጪ አለመመጣጠን ለማስተካከል በማምረቻና በቱሪዝም ዘርፉ ላይ በትኩረት ለመስራት ቅድሚያ ሰጥቶ በመንቀሳቀስ ላይ ነው።

በተለይ በግብርና ላይ የተመሰረተው የወጪ ንግድ በቡና ላይ ጥገኛ ሲሆን የቡና ዋጋ ደግሞ በየጊዜው በመውጣትና በመውረድ የሚፈለገውን የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት አዳጋች አድርጎታል።

የውጭ ባለሃብቶች ወደ አገር ውስጥ የሚያስገቧቸው የግንባታ እቃዎች፣ የተለያዩ መሳሪያዎችና ፣ለማምረቻ የሚጠቀሙባቸው ግብዓቶች በውጭ ምንዛሪ እጥረት ይዘገዩባቸዋል።

ለውጥ ማሳየት ያቃተው የወጪ ንግድ አፈጻጸምና የውጭ ምንዛሪ ክምችቱ በግብርና ላይ ጥገኛ ሆኖ እስከ ቀጠለ ድረስ የገንዘብን የምንዛሪ ዋጋ ዝቅ በማድረግ ወይም የውጭ ምንዛሪ ዋጋን በማሻሻል ብቻ ችግሩን መፍታት አይቻልም።

በአገሪቱ ያለው የዋጋ ግሽበት ከ2012 ዓ.ም ብሄራዊ ምርጫ በፊት ፖሊሲ በማስቀመጥ መላ ሊበጅለት እንደሚገባ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ማሳሰባቸውን ተመራማሪዎቹ አስታውቀዋል።.

ለውጭ ምንዛሪ እጥረቱ በአገር ውስጥ ሃብት የሚከናወኑ (ከሁለቱ የመንግስት ባንኮች የተገኘ) የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ ዝቅተኛ አፈጻጸም አንዱ ምክንያት መሆኑ ተጠቅሷል።

ከዚህ በተጨማሪ የውጭ ብድር ክፍያ፣ ደካማ የሆነው የግብርና አፈጻጸምና የወጪ ንግዱ ስብጥር አለማደግ ምከንያት ናቸው።

መንግስት ነጻ የሆነ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ለመፍጠርና የገንዘብን የመግዛት አቅም ዝቅ ለማድረግ ምክክር ቢያደርግም ወቅቱ ይህንን ለማድረግ እንደማይፈቅድ በመረዳቱ ሀሳቡን ለጊዜው ገታ አደርጎታል።

ምክንያቱ ደግሞ አገሪቷን አሁን የገጠማት ፈተናና የተቃዋሚዎች የምርጫ ዘመቻ እንዲሁም የገንዘብ ግሽበትና የሸቀጦች ዋጋ በተለይ የምግብ ዋጋ (በሰኔ 2019 ግሽበቱ 10 ነጥብ 3 በመቶ) መሆኑ በከፍተኛ ሁኔታ ማሻቀብ ናቸው።

የኒውዮሩኩን የህግ ዳኝነት (አስማሚ አካል) ስምምነት በመቀበል ተግባራዊ ለማድረግና 59 ዓመት ያስቆጠረውን የአገሪቷን የንግድና ኢንቨስትመንት ህግ ከታህሳስ 2012 ዓ.ም በፊት ለማሻሻል እየሰራች መሆኑ በአወንታዊ ጎኑ ከፍ ባለ ደረጃ ሊነሳ የሚችል ተግባር ነው።

ይህም ከንግድ ጋር ተያይዘው የሚነሱ አለመስማማቶችን ለመፍታት ትልቅ እገዛ ያደርጋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በሐምሌ 2011 ዓ.ም በመንግስት የተደነገገውን  “በአገሪቱ ንግድ የማካሄጃ ኢኒሸቲቭ” እውን ለማድረግ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ የሚገኝ ሲሆን ይህንኑ ግብ ከታህሳስ 2012 ዓ.ም ቀደም ብሎ ለማጠናቀቅ ተግቶ እየሰራ ነው።

ጊዜው ያለፈበት የንግድ ህግ የመከለስ ተግባሩ የተጀመረ ሲሆን በቅርቡ እንደሚጸድቅና ይህም የንግድ ባለድርሻዎችን መብት በማስጠበቅ ግልጽነት የተላበሰ የኮርፖሬት አተገባበርን ያሳድጋል።

አገሪቷ የኒውዮርክ ስምምነትን ማጽደቋና የግልግል ዳኝነትን መቀበሏ በኢትዮጵያ የሚገኙ ፍርድ ቤቶች ለውጭ ባለሃብቶች ህጋዊ እውቅና በመስጠት በንግድ ስራ የሚፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታትና የውጭ ባለሃብቶች የሚያቀርቡትን  የካሳ ጥያቄ በውጭ ፍርድ ቤቶች ለማቅረብ እድል ይፈጥርላቸዋል።

ኢትዮጵያ የወጪ ንግዷንና የምርት ስብጥሯን ከግብርና ማላቀቅ ካልቻለችና ከቻይና በተጨማሪ አዳዲስ የንግድ አጋር ማፍራት ካልቻለች ከገጠማት ችግር በፍጥነት ለመውጣት ያዳግታታል።

ከዚህ በተጨማሪ በጊዜ ሂደት የውጭ ምንዛሪ ግብይቱን ለቀቅ ማድረግ እንደሚጠበቅባት ተመላክቷል።

ለውጪ ንግድ አምራቾች ማበረታቻ ማቅረብ፣ ከቀረጥ ነጻ በሆነ መንገድ እቃ ወደ አገር ውስጥ እንዲያስገቡ መፍቀድ የአገር ውስጥ ቁጠባን ማስፋፋትና ፊስካል ፖሊሲውን ጠበቅ ማድረግ አለባት ብለዋል ተመራማሪዎቹ።

ከኤርትራ ጋር የፈጠረችው እርቅ የንግድ ማሳለጫዋን በማስፋት በአሰብና በምጽዋ ወደብ የወጪ ንግዷን ለማሳደግ ያስችላታልም ነው ያሉት ።

ከቱሪዝም ዘርፉ እየመጣ ያለው የውጭ ምንዛሪ በራሱ ተስፋ ሰጪ መሆኑና ወደ አገሪቷ የሚገባው ሬሚታንስ (በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያኖች የሚልኩት ገንዘብ) የችግሩ መፍትሄ ተደርገው ሊወሰዱ ይችላሉ።