ባህርዳር- ጀማ ወንዝ -ፈለገ ብርሃን የአስፓልት መንገድ ግንባታ ተመረቀ

115
መስከረም 8/2012 ከባህር ዳር -ጀማ ወንዝ - ፈለገ ብርሃን የተገነባው 175 ኪሎ ሜትር የኮንክሪት አስፓልት መንገድ ግንባታ የኢፌድሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በተገኙበት ተመረቀ። በአሁኑ ወቅት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ሌሎች የክልልና የፌደራል ከፍተኛ አመራሮች መንገዱን ጎብኝተዋል፡፡ መንገዱ በኢትዮጰያ መንግስት ሙሉ ወጪ በሁለት ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር የተገነባ መሆኑንም የፌደራል መንገዶች ባለስልጣን የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ ተናግረዋል። የመንገዱ መገንባትም የአካባቢውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ከማቃለሉ ባለፈ  ወደ አዲስ አበባ የሚደረገውን ጉዞ በ80 ኪሎ ሜትር ማሳጠር ያስቻለ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ ደረጃውን ጠበቆ የተገነበው ይህው መንገድ በአካባበው በስፋት የሚመረተውን የግብርና ምርት ወደ ማዕከላዊ ገበያ በቀላሉ ለማጓጋዝና ዘመናዊ ተሽከርካሪዎችን ለመጠቀም ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል። መንገዱ የተገነባው በሁለት አለም አቀፍ የቻይና የመንገድ ስራ ድርጀቶች ሲሆን ግንባታው አምስት ዓመት መጨረሱን ተናግረዋል። ከዚህ መንገድ ምረቃ ቀጥሎም ከባህር ዳር ጢስ አባይ የኮንክሪት አስፓልት መንገድ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ የማስቀመጥና የማስጀመር ስራ ይከናወናል ተብሎ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም