በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ባለፈው የትምህርት ዘመን በአካባቢው በነበረው ሁከት ምክንያት ተዘግተው የነበሩ 105 ትምህርት ቤቶች ምዝገባ ጀመሩ

54
መስከረም 8/2012 በማዕከላዊ ጎንደር ዞን አንዳንድ አካባቢዎች ባለፈው ዓመት ተከስቶ በነበረው ሁከት ተዘግተው የነበሩ 105 ትምህርት ቤቶች በዘንድሮው የትምህርት ዘመን ተማሪዎችን ተቀብለው ለማስተናገድ ምዝገባ መጀመራቸውን የዞኑ ትምህርት መምሪያ አስታወቀ፡፡ የመምሪያው ሃለፊ አቶ መስፍን እርካቤ ለኢዜአ እንደገለፁት ባለፈው ዓመት በአካባቢው ተፈጥሮ በነበረ የፀጥታ ችግር ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ስራ አቋርጠው ከርመዋል። በዚህ ዓመት ግን ሰላማዊ የመማር ማስተማር እንዲሰፍን እስከ ቀበሌ ድረስ ከማህበረሰቡ ጋር በመወየያት ማስተማር አቋርጠው የነበሩ 100 የአንደኛና አምስት የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መደበኛ ስራቸውን ይጀምራሉ። በፀጥታ ምክንያት ሙሉ በሙሉ ቃጠሎ ደርሶባቸው የነበሩ ሰባት ትምህርት ቤቶች በመንግስትና በህበረተሰቡ ድጋፍ እንደገና ተገንብተው ለአገልግሎት መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል። ለትምህርት ተቋማቱ መምህራንን በመመደብና ወንበርና ሌሎች ለመማር ማስተማር የሚያግዙ ቁሳቁሶች ተሟልተው የምዝገባ ስራ የተጀመረ ሲሆን በቀጣይ መስከረም 12 መደበኛ ትምህርት መስጠት እንደሚጀምር ተናግረዋል፡፡ በየትምህርት ቤቶቹ አካባቢ ያለው ህብረተሰብም ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር ከማድረግ በተጨማሪ አምስት ሚሊዮን ብር የሚገመት የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉንም አብራርተዋል። በዞኑ ጭልጋ ቁጥር1 ወረዳ የአይከል 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር ጋሻው አማረ በበኩላቸው ባለፈው አመት የተፈጠረው ክስተት የትውልድ መቅረጫ የሆኑ የትምህርት ተቋማት መውደማቸው አሳዛኝ ነው፡፡ ካለፈው ተሞክሮ በመውሰድም በዚህ ዓመት ሰላማዊ የመማር ማስተማር እንዲሰፍን በተማሪዎች፣ በመምህራንና በህዝቡ በጋራ ለሰላም እንዲሰራ እየተደረገ ይገኛል። ‹‹እኛ ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታ የሚያርቅና ላልተገባ ሁከትና ብጥብጥ የሚዳርግ እንድም ምክንያት ሊኖር አይገባም፤›› ያለው ደግሞ በአይከል መሰናዶ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ ሙሉቀን ሲሳይ ነው፡፡ በተያዘው አመት ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም የመግባት አላማውን ያከሸፈበት ህገ-ወጥ ድርጊት ዳግም እንዳይከሰትም ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ተማሪውንና ህዝቡን የማንቃት ስራ እየሰራ መሆኑንም ተናግሯል፡፡ ‹‹ትምህርት በመቋረጡ የተመለሰ ጥያቄ የለም ነገር ግን ብዙ ተማሪዎች በሁከትና ብጥብጡ በመሳተፋቸው ህይወታቸው እንዲያልፍና የአካል ጉዳት እንዲደርስባቸው አድርጓል፤›› ያለቸው ደግሞ በአይከል ከተማ የሰራቆ 1ኛ ደረጃ ትምርት ቤት የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ራሄል ፀጋው ናት፡፡ በመሆኑም መንግስትና ህዝቡ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ተግባር እንዲኖር መስራት እንደሚገባቸው ተናግራለች፡፡ ባለፈው አመት ከ3ሺህ በላይ መምህራንና ከ60 ሺህ በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ርቀው መቆየታቸው ታውቋል። በዞኑ ባሉ በ147 የመጀመሪያና በ47 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከ163 ሺህ በላይ ተማሪዎች እንደሚማሩ ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም