በከተማው የመሰረተ ልማት ግንባታ ሊካሄድ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በከተማው የመሰረተ ልማት ግንባታ ሊካሄድ ነው
87
መስከረም 8/2012 የነቀምቴ ከተማ አስተዳደር በተያዘው የበጀት ዓመት ከ102 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የተለያዩ የመሠረተ ልማት ስራዎችን ለማከናወን አቅዶ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ፡፡ የአስተዳደሩ ማዘጋጃ ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ቶለሳ ደጋጎ እንደተናገሩት ከተማ አስተዳደሩ የህብረተሰቡን የመሰረተ ልማት ጥያቄ ለመመለስ በበጀት ዓመቱ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል፡፡ በዓመቱ ለማከናወን በእቅድ ከተያዘው የልማት ስራ ውስጥ የ7 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የኮብል ድንጋይ ንጣፍ መንገድና የ8 ነጥብ 3 የጎርፍ መቀልበሻ ቦይ ስራ ይገኙበታል፡፡ እንዲሁም የሁለት መካከለኛ ድልድዩች ግንባታ፣ የ2 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር አዲስ የውሃ መስመር ዝርጋታ፣ የ5 ሸድ ስራዎች እና የአንድ ቆሻሻ ማንሻ ተሽከርካሪ ግዥ እንደሚከናወን ገልፀዋል፡፡ አቶ ቶለሳ እንዳሉት ከተማ አስተዳደሩ ዘንድሮ ከሚያከናውነው የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ጎን ለጎን በከተማው የሚታየውን የኪራይ ሰብሳቢነትና ሕገ ወጥ ግንባታ መስመር ለማስያዝ በትኩረት ይሰራል፡፡ ለግንባታው ስኬታማነት ህብረተሰቡ በገንዘቡም ሆነ በጉልበቱ ኣስተዋጽኦ ማድረግ እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡