በወላይታ ዞን በደረሰ የትራፊክ አደጋ የሶስት ሰዎች ህይወት አለፈ

123
ሶዶ /ኢዜአ/ መስከረም 7/2012 በወላይታ ዞን በቦሎሶ ሶሬ ወረዳ አንድ መለስተኛ የህዝብ ማመላለሻ አዉቶብስ ተገልብጦ የሶስት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ በ20 ሰዎች ላይ ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት መድርሱን የወረዳው ፖሊስ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ። በጽህፈት ቤቱ የትራፊክ አደጋ መከላከልና ቁጥጥር ዋና የስራ ሂደት አስተባባሪ ሳጂን አዳነ አሰፋ ለኢዜአ እንደገለጹት አደጋው የደረሰው መለስተኛ የህዝብ ማመላለሻ አውቶብሱ በወረዳው ዋሙራ በሚትባል የገጠር ቀበሌ አካባቢ ተገልብጦ ወንዝ ውስጥ በመግባቱ ነው። የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3- 4147 ደ.ህ የሆነው ይህ አውቶብስ ከአረካ ወደ ማዞሪያ 29 መንገደኞችን አሳፍሮ ሲጓዝ በደረሰበት የመገልበጥ አደጋ ከሟቾቹ በተጨማሪ ሶስቱ ከባድ የመቁሰል አደጋ ሲደርስባቸው አሽከርካሪውን ጨምሮ ሌሎች 17ቱ ደግሞ ቀላል የመቁሰል አደጋ እንደደረሰባቸው ገልጸዋል። ዛሬ ከቀኑ 10 ሰዓት ገደማ በደረሰው በዚህ አደጋ የቆሰሉ መንገደኞች በዱቦ ማሪያም ሆስፒታል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸዉ መሆኑን ገልጸው የሟቾቹ አስከሬን ለቤተሰቦቻቸው መሰጠቱን ተናግረዋል። የአደጋው መንስኤ እየተጣራ እንደሚገኝ የገለጹት ሳጅን አዳነ አካባቢው ቁልቁለታማ በመሆኑ አሽከርካሪዎች የመንገድ አጠቃቀም ስርዓትን አክብረው በጥንቃቄ ሊጓዙ እንደሚገባ አሳስበዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም