ጨዋታውን በድል ለመወጣት ተዘጋጅተናል --- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ አብረሃም መብራህቱ

96
መቀሌ ኢዜአ መስከረም 7/2012፡- የኢትዮጵያ የእግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን በመጪው እሁድ ከሩዋንዳ አቻው ጋር የሚካሄደው የማጣሪያ ጨዋታ በድል ለመወጣት የስነ ልቦናና የአካል ዝግጅት ማድረጋቸውን የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ አብረሃም መብራህቱ ገለጹ። ብሔራዊ ቡድኑ ከሩዋንዳ አቻው ጋር የሚካሄደው  እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ2020 ካሜሮን  ለሚካሄደው የቻን አፍሪካ ውድድር ለማለፍ ነው። ለዚህም ዝግጅት ብሔራዊ ቡድኑ ልምምዱን በትግራይ ዓለም አቀፍ ስታድዮም እያደረገ ነው። የቻን አፍሪካ  ውድድር በሀገር ውስጥ ፕሪሜየር ሊጎች ብቻ የሚጫወቱ ስፖርተኞችን የሚሳተፉበት እንደሆነ ተመልክቷል። የብሔራዊ ቡድኑ  አሰልጣኝ አብረሃም መብራህቱ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት ጨዋታው በድል ለመወጣት የስነ ልቦናና የአካል ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል። ቡድኑ ውድድሩን በድል ለመወጣት በትግራይ አለም አቀፍ ስቴድዮም ልምምዳቸውን በተሟላ መንገድ እያካሄዱ መሆናቸውን ገልጸዋል። የብሔራዊ ቡድኑ አባላት ጤንነት ፣በአካልና በስነ ልቦና ዝግጅት  በመልካም ሁኔታ እንደሚገኙ አስታውቀዋል። ተጨዋቾቹ መቀሌ ከተማ ሲደርሱ በአከባቢው ነዋሪዎች፣በክልሉ መንግስትና በፕሪሜየር ሊግ አሰልጣኞች  ደማቅ አቀባበል እንዳደረጉላቸው አስለጣኝ አብረሃም ተናግረዋል። እንደ አቀባበሉ ሁሉ በመጪው እሁድ  ከሩዋንዳ ብሄራዊ ቡድን ጋር  በሚያደርጉት ጨዋታ ወቅት  በድጋፉም እንዲደገም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል" ከብሔራዊ  ቡድኑ ተጨዋቾች  መካከል ሃይደር ሸረፋ በሰጠው አስተያየት "አሸንፈን ለመውጣት ሙሉ ዝግጅት አድርገናል" ብለዋል። የመቀሌ ከተማ ነዋሪ ህዝብ በጨዋታው እለትም  የተለመደውን ስፖርታዊ ጨዋነት የተላበሰ ድጋፉን እንዳይለያቸውም አመልክቷል። የትግራይ ዓለም አቀፍ ስቴዲዮም ደረጃውን የጠበቀና የተመቸ ከመሆኑ በተጨማሪ አሸንፈው ለመውጣት የስነ ልቦና ዝግጅትና ብቁ ልምምድ  ማድረጋቸውን የገለጸው ደግሞ ሌላው የብሔራዊ ቡድኑ አባል ከነአን ማርክነህ ነው። በመጪው እሁድ መቀሌ በሚገኘው የትግራይ ስቴዲዮም ከሩዋንዳ ጋር በሚካሄደው ውድድር ጥሩ ተፎካካሪ በመሆን በአሸንፈነት  ለመወጣት የተሟላ ዝግጅት ማድረጋቸውን የቡድኑ አባላት ተናግረዋል።                                
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም