ለሁሉም ክፍት የሆነው የወርልድ ቴኳንዶ ውድድር ዛሬ ተጀመረ

68

መስከረም 7/2012  ለሁሉም ክፍት የሆነው የወርልድ ቴኳንዶ ውድድር ዛሬ ቦሌ በሚገኘው የብሔራዊ ስፖርት ፌዴሬሽኖች ጂምናዚየም ተጀምሯል።  በውድድሩ መጀመሪያ ቀን ሶስት የፍጻሜ ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

በውድድሩም ከዘጠኙ ክልሎችና ከሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ 150 ተወዳዳሪዎች  እንደሚሳተፉ ተገልጿል።

በሴት ከ49፣ 57 እና 67 ኪሎ ግራም በታች እንዲሁም በወንድ ከ58፣ 60 እና 80 ኪሎ ግራም በታች ውድድሩ የሚካሄድባቸው የክብደት ዘርፎች ናቸው።

የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ፍቅሩ ተቋም ለኢዜአ እንደገለጹት በውድድሩ ላይ የተሻለ ብቃት ያሳዩ ተወዳዳሪዎች ተመርጠው እ.አ.አ በ2020 በሚካሄደው የቶኪዮ ኦሊምፒክ ለመሳተፍና በጥር 2012 ዓ.ም ሞሮኮ ላይ በሚካሄደው የማጣሪያ ውድድር ላይ የሚሳተፈው ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ይካተታሉ።

በሁለቱም ጾታዎች በተመሳሳይ አምስት ተወዳዳሪዎች እንደሚመረጡና ከመስከረም 20 ቀን 2012 ዓ.ም በኋላ ስድስት ነባር ስፖርተኞችን ከያዘው የወርልድ ቴኳንዶ ብሔራዊ ቡድን ጋር ተቀላቅለው ልምምድ ማድረግ እንደሚጀምሩም ተናግረዋል።

ስፖርተኞቹም በልምምድ ወቅት ከአሰልጣኞች በሚሰጠው ስልጠና እና በልምምዱ ተጣርተው ወቅታዊ ብቃትን መሰረት ባደረገ መልኩ ተመርጠው ሞሮኮ በሚካሄደው የኦሊምፒክ የማጣሪያ ውድድር እንደሚሳተፉም አመልክተዋል።

ውድድሩ ሞሮኮ ከሚካሄደው የማጣሪያ ውድድር ባለፈ ለስፖርተኞች የውድድር አማራጭ ከመፍጠርና ልምድ እንዲያገኙ ከማድረግ አኳያ ያለው ሚና ወሳኝ መሆኑን ነው አቶ ፍቅሩ ያስረዱት።

በቀጣይም በዚህ ዓመት ለሁሉም ክፍት የሆነው የወርልድ ቴኳንዶ ውድድር በጥር  2012 ዓ.ም እንደሚካሄድም ጠቁመዋል።

ዛሬ በውድድሩ መጀመሪያ ቀን በሴት ከ57 እና ከ67 ኪሎ ግራም በታች እንዲሁም ከ68 ኪሎ ግራም በታች ወንድ የፍጻሜ ውድድሮች የሚካሄዱ ይሆናል።

በተወሰኑ ጨዋታዎች በተወዳዳሪዎች በኩል ተመጣጣኝ ፉክክር ያለመኖር፣ የተወሰኑ ተወዳዳሪዎች ነጥብ ለማስቆጠር የሚጠቀሙበት ቴክኒክ ድክመት ያለበት መሆኑና የተወዳዳዳሪዎች የማጥቃትና የመከላከል ስልት የአቅም ችግር የሚታይበት መሆኑን ለመመልከት ተችሏል።

በተጨማሪም ከውድድሩ ተሳታፊዎች ውጪ በውድድሩ ስፍራ ተገኝቶ ጨዋታዎቹን ሲመለከቱ የነበሩ ተመልካቾች ቁጥርም በጣም አነስተኛ ነው።

ውድድሩ እስከ መስከረም 9 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ ይቆያል።