በክረምት ወቅት የተተከሉ ችግኞችን የመንከባከብ ስራ እየተካሄደ ነው

65
መስከረም 07/2012 በአማራ ክልል በክረምቱ ወቅት የተተከለውን ከአንድ ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ ችግኝ የፅድቀት መጠን ለማሳደግ ሚያስችል የእንክብካቤ ስራ እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ። የቢሮው የደን ልማት ባለሙያ አቶ እስመለዓለም ምህረት ትላንት ለኢዜአ እንደገለጹት የተተከለውን ችግኝ ጽድቀት መጠን ማሳደግ በአገር ደረጃ የተያዘውን አረንጓዴ ልማት ግብ ለማሳካት ሚናው የጎላ ነው። በዚህም በክረምቱ ወቅት በወል፣ በግልና በተቋማት የተተከለው ከአንድ ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ ችግኝ የአረም፣ የኩትኳቶና የመንከባከብ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኝ አስረድተዋል። እስካሁን በተደረገው ጥረትም 500 ሺህ የሚጠጋ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ ከግማሽ ቢሊዮን በላይ በሚሆኑ ችግኞች የመንከባከብ ስራ መከናወኑን አስታውቀዋል። በየአባቢው የሚገኙ አረጋውያንና የሃይማኖት አባቶችም ያላቸውን ልምድ በመጠቀም  ህብረተሰቡን በመቀስቀስና በማነሳሰሳት ግንባር ቀደም ሚና በመጫዎት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል። የተተከለውን ችግኝ በመንከባከብ ረገድም ቆላማ በሆኑ የክልሉ አካባቢዎች ካለፈው ነሓሴ 22 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ እየተከናወነ ሲሆን ዝናብ በሚበዛባቸው እንደ ደጋና ወይና ደጋ ባሉ አካባቢዎች ደግሞ ከጳጉሜ ጀምሮ መከናወኑን ተናግረዋል። ምዕራብ ጎጃም ዞን ሰከላ ወረዳ የኮለል ለቻ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አማረ ላቀ እንዳሉት ቡገታ በሚባለው ተፋሰስ በክረምት ወቅት የተተከለውን ከ30 ሺህ በላይ የደን ችግኝ ህብረተሰቡን በማስተባበር የአረምና ኩትኳቶ ስራ ማከናናቸውን ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት በአካባቢው እየጣለ ያለው ዝናብ የተተከለው ችግኝ በቀላሉ ለማረምና ኮትኩቶ ለማሳደግ አመቺ ሁኔታ መፍጠሩንም አስረድተዋል። በቀበሌያቸው የሚገኘውን የተራቆተ ተራራማ መሬት በክረምት ወቅት ህብረተሰቡ በነቂስ ወጥቶ የተከለውን ችግኝ እየተንከባከበ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በባህርዳር ዙሪያ ወረዳ የደብረፅዮን ላጉና ቀበሌ አርሶ አደር አድማስ አበበ ናቸው። እሳቸውን ጨምሮ ህብረተሰቡ የተከለውን ችግኝ ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ በመጠበቅ፣ በማረምና በመኮትኮት እየተንከባከበ ያለው ደን የሚያስገኘውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እየተረዳ በመምጣቱ ነው። የክልሉ ውሃ መስኖና ኢነርጂ ሃብት ልማት ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አደም ወርቁ በበኩላቸው ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም በአባይ ማዶ ቤዛዊት ቤተመንግስት በተረክቡት መሬት የተከሉትን ችግኝ የመንከባከብና የደረቁትን የመተካት ስራ መስራታቸውን ገልጸዋል። በሚቀጥለው ሳምንት ደግሞ ሁሉም ሰራተኞች በነቂስ ወጥተው በአረንጓዴ አሻራ ቀን የተከሉትን ችግኝ በማረምና በመኮትኮት የመንከባከብ ስራ እንዲያከናውኑ ዝግጅት መደረጉንም አስረድተዋል። በክረምቱ ወቅት ከተተከለው ችግኝ ውስጥም 82 ነጥብ 2 ሚሊዮን የሚሆነው ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ በጠሩት የአረንጓዴ አሻራ ቀን የተተከለ መሆኑንም ጠቅሰዋል። በክልሉ ባለፈው ዓመት የክረምት ወቅት ከተተከለው ከአንድ ነጥብ ሰባት ቢሊዮን በላይ ችግኝ 64 በመቶ የሚሆነው ፀድቆ በጥሩ ሁኔታ እንደሚገኝም ከቢሮው የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም