አምስት የስፖርት ማዘዉተሪያ ስፍራዎች ተጠናቀው ለአገልግሎት በቁ

122
መስከረም 7/2012 በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ከ67 ሚሊዮን ብር በላይ በመገባት ላይ ከነበሩት የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች መካከል አምስቱን በማጠናቀቅ ለአገልሎት ማብቃቱን የዞኑ ስፖርት መምሪያ አስታወቀ። በመምሪያው የስፖርት ማዘዉተሪያና ማእከላት ማስፋፊያ ባለሙያ ወይዘሮ ህይወት ታደሰ ለኢዜአ እንደገለጹት በስፖርቱ ዘርፍ ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን መሰረታዊ ችግሮች ለመቅረፍ እየተሰራ ነው፡፡ በዚህም ባፉት ዓመታት ከ67 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጭ በ13 ወረዳዎች ግንባታቸው በመካሄድ ላይ ካሉት  የስፖርት ማዘውተሪያዎች መካከል የአምስቱ ተጠናቆ ለአገልግሎት መብቃቱን ገልፀዋል። ግንባታቸው ተጠናቆ ለአገልግሎት የበቁት የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችም በአጣዬ፣ በመንዝ ቀያ፣ በአንጾኪያ ገምዛና በደብረ ብርሃን ከተማ የሚገኙ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎቹ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ፍላጎታቸው እየጨመረ የመጣውን የባህላዊ ስፖርት ጨዋታዎችና ዘመናዊ ስፖርቶችን ለማስፋፋት የሚኖራቸው ፋይዳ የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ቀሪዎቹ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍዎችን ለማጠናቀቅም ከወረዳዎችጋር በመመካከር እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ የሸዋ ሮቢት ከተማ አስተዳደር ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ብሌን ብርሃኑ በበኩላቸዉ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከተማቸው የስፖርት ተሳታፊዎች ቁጥር እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል። የህብረተሰቡን ፍላጎት በመረዳትም መስተዳድራቸው ባለፈው ዓመት ያስጀመረውን የስፖርት ማዘውተሪያ ግንባታ ሁለት ነጥ ሁለት ሚሊዮን ብር በመመደብ በሁለት ወራት ውስጥ አጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃት ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የሸዋ ሮቢት ከተማ ነዋሪ ወጣት ጋሻዉ መክቴ በሰጠው አስተያየት የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራው መገንባት ወጣቱ ለሚያደርገው ስፖርታዊ እንቅስቃሴ መጠናከር አመች ሁኔታ እንደሚፈጥር አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም