የመስቀል በዓልን ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀ የስፖርት ውድድር በአዲግራት ከተማ ተጀመረ

66
መስከረም 6/2012 በዓዲግራት ከተማ የፊታችን መሰከረም 17 የሚከበረውን የመስቀል በዓል ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀ የስፖርት ውድድር ዛሬ ተጀመረ። የትግራይ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ቢሮ የስፖርት ፌስቲቫል ባለሙያ አቶ ሙሉጌታ ብስራት ለኢዜአ እንደገለፁት ውድደሩ በ7 የስፖርት ዓይነቶች የሚካሄድ ነው። "አትሌቲክስ፣ ብስክሌት፣ የእግርና መረብ ኳስ ከውድድር አይነቶቹ ተጠቃሽ ናቸው" ብለዋል ። በዛሬው እለው አዲግራት ከተማን መነሻና መድረሻ ያደረገና ከዓዲግራት - ሃውዜን የ120 ኪሎ ሜትር የወንዶች ብስክሌት የደርሶ መልስ  ውድድር  ፍፃሜ አግኝቷል። በግልና ከአራት ክለቦች የተውጣጡ ከ40 በላይ ኮርሰኞች ውድድሩን  በ3፣00 ሰዓታት ውስጥ አጠናቀዋል ። ከትራንስ ኢትዮጵያ ዛይድ ተስፉ ውድደሩ በአንደኛነት ሲያጠናቅቅ ከጉና ንግድ ስራዎች አክስዮን ማህበር ፍሰሃ ገብረመድህንና ኃይለመለኮት ወልደአበዝጊ ሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃ በመያዝ አጠናቀዋል ። በክለብ ደረጃ በአጠቃላይ ውጤት ጉና፣ትራንስ ኢትዮጵያና መሰቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ  ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ በመያዝ ዋንጫና ሜዳልያ ተሸልመዋል ። በሌላ በኩል በ3ሺህ ሜትር የሴቶች ሩጫ አጽቢወንበርታ ወረዳን ወክለው የቀረቡ ወጣት መብርሂት ገብረ፣ ተኽለ ካህሳይና ለታይ ገብረእግዚአብሄር እንደየቅደም ተከተላቸው ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ በመያዝ የሜዳሊያ ተሸላሚ ሆነዋል ። በወንዶች በተካሄደ ተመሳሳይ ውድድር አጽቢ ወንበርታ ወረዳን ወክለው የቀረቡ ወጣት በሪሁ ገብረመድህንና ወጣት አማኑኤል ወልአዛር 1ኛና 3ኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቀዋል ። ውድድሩን 2ኛ በመሆን ያጠናቀቀው ደግሞ ሳእስዕ ጻዕዳ አምባ ወረዳን ወክሎ የቀረበው ወጣት ሰናይ መሰለ ነው። የመስቀል በዓልን ምክንያት በማድረግ ዛሬ የተጀመረው የሰፖርት ውድድር መስከረም 16 ቀን 2012 ዓም እንደሚጠናቀቅ ታውቋል ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም