በክልሉ የተጀመረው ለውጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እየተሰራ ነው

91

መስከረም 6/2012 በአፋር ክልል የህብረተሰቡን ሰላም በዘላቂነት በማስጠበቅ የተጀመረው ለውጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ገለፀ፡፡

ለክልሉ ፖሊስ ከፍተኛ አመራሮች የተዘጋጀ የአምስት ቀናት ስልጠና ዛሬ በሰመራ ከተማ ተጀምሯል፡፡

በስልጠናው መክፈቻ ላይ የቢሮው ኃላፊ አቶ አህመድ መሃመድ እንደተናገሩት በክልሉ የተጀመረው ለውጥ የህብረተሰቡን ሰላምና የህግ የበላይነትን ባረጋገጠ መልኩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እየተሰራ ነው፡፡

ለዚህም ይረዳ ዘንድ የክልሉ ጸጥታ አካላት በተለይም የፖሊስ ሃይሉ ለውጡን  መሸከም በሚችልበት መንገድ እንዲደራጅ በማድረግ የስነ-ምግባርና ተያያዥ ችግሮች ለመቅረፍ የሚያስችሉ ተቋማዊ ሪፎርም በመካሄድ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

ሪፎርሙም እስከታችኛዉ አስተዳደር እርከንና የፖሊስ አባል ድረስ በአግባቡ ለማውረድ አስፈላጊው ስራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡

በመሆኑም ክልሉ የሚታወቅበትን የህዝቦች አብሮነት ተጠናክሮ እንዲቀጠል በማድረግ በኩል የፖሊስ አባላቱ የህግ የበላይነት በማያወላዳ መልኩ በማረጋገጥ ህዝብና መንግሰት የጠለባቸዉን ሃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ አሳስበል፡፡

አፋር ክልል ፖሊስ ኮሚሸን ኮሚሽነር አሊ ዲኒ አለሳ በበኩላቸዉ በተያዘው የበጀት አመት  በተጀመረዉ ተቋማዊ የሪፎርም ስራ ከህግ ማእቀፍ ጀምሮ ወቅቱ የሚጠይቀውን ብቃትና ክህሎት የተላበሱ የፖሊስ አመራሮችን በመመደብ የተሻለ የህዝብ አግልጋይነት ስሜት የተላበሰ ፖሊስ ለመገንባት ጥረት እየተደረገ ነዉ፡፡

የተጀመረዉ ሪፎርም ለዘመናት በተቋሙ ዉስጥ የነበሩ የአሰራረና የስነ- ምግባር ብልሽቶችን ደረጃ በደረጃ ለመቅረፍ በየግዜው ችግሮችን እየፈተሸ አባላቱን እያጠራ አስፈላጊዉን የመፍትሄ እርምጃዎች እየወሰደ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡

ስልጠናው በተቋሙ የተጀመረው ሪፎርም ያስገኘው ስኬትና ክፍተቶች እንዲሁም ሰብአዊና ዴሞክራሲዊ መብቶች በፌዴራሊዝምና የህግ የበላይነት በሚሉ ርእሶች ላይ የሚያጠነጥን ነዉ፡፡

በስልጠናው ላይ ከዞንና ከወረዳ የተውጣጡ ከ250 በላይ የክልሉ ፖሊስ አመራር አካላት ተሳታፊ ሆነዋል፡፡