በአማራ ክልል በህገወጥ መንገድ ተወስዶ የነበረ የአቅመ ደካሞችና የወል መሬት ማስመለስ ተቻለ

79
መስከረም 6/2012 በአማራ ክልል በህገወጥ መንገድ ተወስዶ የነበረ 14 ሺህ 822 ሄክታር የአቅመ ደካሞችና የወል መሬት በህግ ማስመለስ መቻሉን የክልሉ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ቢሮ ገለጸ። የቢሮው የመሬት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ጌታሁን አለምነህ ለኢዜአ እንደገለጹት በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ከተመለሰው ከዚሁ መሬት ውስጥ ከ7 ሺህ 300 የሚበልጡ ወላጆቻቸውን በሞት ያጡ ህፃናት፣ የአረጋዊያንና አካል ጉዳተኞች ይዞታ የነበረ አንድ ሺህ 300 ሄክታር መሬት ይገኝበታል። ቀሪው የወል መሬት መሆኑንም ገልፀዋል። ግለሰቦቹ መሬታቸውን ያለአግባብ ተነጥቀው ለችግርና እንግልት ተዳርገው መቆየታቸውን ጠቅሰው፤  በአሁኑ ወቅት መሬታቸውን ተረክበው አልምተው እንዲጠቀሙ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። በአዲሱ የበጀት ዓመትም እስካሁን በህገ ወጥ መንገድ ተይዞ ያልተመለሰ 15 ሺህ ሄክታር መሬት በህግ አግባብ ለማስመለስ እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በባህር ዳር ዙሪያ ወረዳ የወንጀጣ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ወይዘሮ አዘን የእኔዓለም በሰጡት አስተያየት ቀደም ሲል ሩብ ሄክታር የእርሻ መሬት በአንድ ግለሰብ በመነጠቃቸው ሲቸገሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል። ግሰለሰቡ የነጠቃቸውን መሬት በአካባቢው ህብረተሰብ ዕገዛ የመሬት ይዞታቸውን በፍርድ ሂደት ውሳኔ አግኝቶ እንዲመለስላቸው መደረጉንም አስረድተዋል። በወረዳው የላታ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ወርቅነሽ አብች በበኩላቸው ግማሽ ሄክታር መሬት በሰብል ተጠምደው ሲያርሱ የነበሩ ግለሰቦች መሬቱ የራሴ ነው በሚል በመቀማታቸው ለችግር ተዳርገው እንደቆዩ ተናግረዋል። ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ እስካሁን ሩብ ሄክታር የሚሆነውን መሬት ተመልሶላቸው አከራይተው መጠቀም እንደቻሉ አመልክተው፤ቀሪውን ሩብ ሄክታር መሬት ደግሞ በፍርድ ሂደት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም