በኢትዮጵያ የቲቢ እና ወባ በሽታዎች ስርጭት እየቀነሰ መምጣቱ ተገለፀ

113

መስከረም 6/ 2012 በኢትዮጵያ የቲቢ እና ወባ በሽታዎች ስርጭት እየቀነሰ መምጣቱ ተገልጿል።

በመጪው ጥቅምት ወር በፈረንሳይ የሚካሄደውን 6ኛው የግሎባል ፈንድ ገንዘብ ማሰባሰቢያ ኮንፍረንስን አስመልክቶ ትናንት ምሽት በአዲስ አበባ ፈረንሳይ ኤምባሲ ውይይት ተካሂዷል።

ግሎባል ፈንድ ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የቲቢን፣ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስንና ወባ በሽታዎችን ለመከላከል ዓለም አቀፍ ድጋፍ እያደረጉ ካሉት ተቋማት መካከል ግንባር ቀደሙ ነው።

ፈንዱ ለጋሽ አገራት ለጤናው ዘርፍ በተለይም ለቲቢ፣ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስና ወባ ህክምናን ለማጠናከር በአንድ ቋት የገንዘብ ድጋፍ የሚሰጡበት ፈንድ ነው።

የውይይት መድረኩ የተዘጋጀውም ግሎባል ፈንድ የሚያከናውነውን ሥራ ማጠናከር ይችል ዘንድ ዓለም አቀፍ ለጋሽ አካላት አስፈላጊውን የገንዘብ ድጋፍ እንዲሰጡ ለማሳሰብ ነው።

በውይይቱ ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ሊያ ታደሰ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለፁት፤ኢትዮጵያ ከግሎባል ፈንድ ዋነኛ ተጠቃሚ አገር መሆኗን ተናግረዋል።

በዚህም በተለይም ባለፉት 15 ዓመታት በተገኘው ድጋፍ የቲቢ፣ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስና ወባ  ህክምናን በማስፋፋት መድሃኒት በማቅረብ፣ በሽታዎቹን በመከላከልና በመቆጣጠር ዙሪያ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።

ይህንን ተከትሎም በርካታ ለውጦች ተመዝግበዋል ያሉት ዶክተር ሊያ ለአብነትም በወባ የሚሞቱ ሰዎች 80 በመቶ መቀነሱን፡ በሳንባ ነቀርሳ የመያዝ መጠን 40 በመቶ መቀነሱን እና እንዲሁም በኤች አይቪ ምክንያት የሚከሰተው ሞት ከ70 በመቶ በላይ መውረዱን ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ አሁንም የሚቀሩ ስራዎች አሉ ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ በቀጣይ የበሽታዎቹን ስርጭት  ለመቆጣጠር መንግስት ትኩረት አድርጎ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ለዚህም ደግሞ ከጤና ኤክስቴንሽን እስከ ህክምና ተቋማት የሚሰጠውን አገልግሎት ጠንካራ የማድረግ እና ከለጋሽ አገራት ከሚሰጠው ድጋፍ ባሻገር በራስ አቅም ጠንካራ የጤና ስርዓት ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የግሎባል ፈንድ ተወካይ ወይዘሮ ሹሹ ተክለሀይማኖት በበኩላቸው በኢትዮጵያ በተለይ በቲቢ፣ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስና ወባ  በሽታዎች ላይ በተሰራው ጠንካራ ስራ ለውጥ ማምጣት ተችሏል ሲሉ ተናግረዋል።

ወደፊትም ከህክምና ተቋማት ተደራሽነት ባሻገር ጥራት ያለው የአገልግሎት ላይ ትኩረት ተደርጎ ሊሰራ እንደሚገባም አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ፍሬድሪክ ቦንተንስ እንዳሉት ደግሞ ፈረንሳይ ለግሎብል ፈንድ ሁለተኛዋ ግዙፍ ለጋሽ አገር መሆኗን ጠቅሰው ኢትዮጵያም በተዘዋዋሪ ከዚህ ድጋፍ ዋነኛ ተጠቃሚ መሆኗን ተናግረዋል።

የቲቢ፣ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስና ወባ በሽታዎችን ለመከላከል የሚያስፈልገውን ኃብት ለማቅረብ የተቋቋመው ግሎባል ፈንድ በየዓመቱ ከ4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ በማሰሰባሰብ ከ100 በላይ አገራት በሽታዎቹን ለመከላከል የሚያደርጉትን ጥረት እየደገፈ ያለ ዓለም አቀፍ ተቋም ነው።