ኢትዮጵያ በ63ኛው የዓለም የአቶሚክ ኢነርጂ ጉባኤ ላይ እየተሳተፈች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በ63ኛው የዓለም የአቶሚክ ኢነርጂ ጉባኤ ላይ እየተሳተፈች ነው
አዲስ አበባ መስከረም 6/2012 ኢትዮጵያ በኦስትሪያ እየተካሄደ ባለውና የአቶሚክ ኢነርጂን ለምጣኔ ኃብታዊ እድገት በስፋት መጠቀም በሚቻልበት መንገድ ላይ በሚመክረው የዓለም አቶሚክ ኢነርጂ ጉባኤ ላይ እየተሳተፈች ነው። በኦስትሪያ ርእሰ መዲና ቪዬና ትናንት የጀመረውና ለአራት ቀናት የሚቆየው ጉባኤው የአቶሚክ ኢነርጂን ለኃይል ማመንጫ፣ ለግብርና ልማትና የጤና አገልግሎቶችን ጨምሮ ለአጠቃላይ ሳይንስና ቴክኖሎጂ እድገት መጠቀም በሚቻልበት መንገድ ላይ ይመክራል። እንደዚሁም ዘርፉን ከሰላማዊ ዓላማ ውጭ ከመጠቀም ለመቆጠብ መንግስታት የገቡትን ቃል ኪዳን የበለጠ ለማክበር ያላቸውን ቁርጠኝነት ማጠናከር በሚችሉበት ስልት ላይም ይነጋገራል ተብሏል። በጉባኤ ላይ ኢትዮጵያን በመወከል የተሳተፉት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ የጨረራ ባለስልጣንና ሌሎች የሚመለከታቸው ኃላፊዎች ናቸው። የኢኖቬሽንና ቴክኖለጂ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ አለምነው ለኢዜአ እንደገለጹት ኢትዮጵያ የጉባኤው ተሳታፊ የሆነችው የአቶሚክ ኢነርጂ አባል አገርና በዘርፉ በፈረመቻቸው ስምምነቶች መሰረት ነው። ኢትዮጵያ የአቶሚክ ኢነርጅን ለሰላማዊ አገልግሎትና ለምጣኔ ኃብታዊ ልማት ብቻ ለመጠቀም ቀደም ሲል ስምምነት መፈረሟንም አውስተዋል። እየተካሄደ ባለው ጉባኤ ላይም ኢትዮጵያ ዘርፉን ለምጣኔ ኃብታዊ ልማት፣ ለሳይንስና ቴክኖሎጂ እድገት መጠቀም የምትችልበትን አቋም ታንጸባርቃለች። ይህም በዘርፉ ተጨማሪ ስምምነነቶችን ለመፈረምና ፈቃድ ለማግኘት ያስችላታል ነው ያሉት። የአቶሚክ ኢነርጂ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው ለኤክስሬይና ለጨረር ህክምና ብቻ መሆኑን ገልጸዋል። እንደ ኃላፊው ገለጻ የጨረር አመንጪ ቁሶችን በመቆጣጠርና በመከታተል ለኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ለማዋል በኢትዮጵያ ጨረራ ባለስልጣን አማካኝነት ስራዎች እየተከናወኑ ነው። የገንዲ በሽታን ለመከላከል፣ ለህክምና ቴክኖሎጂና ሌሎች የኃይል አማራጮችን ለማግኘት የጨረር ኃይልን ጥቅም ላይ ለማዋል ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አክለዋል። ጨረር የሚያመነጩ ቁሶችና ያለአግባብ ጨረር የሚጠቀሙ ንጥረ ነገሮች ወደአገር እንዳይገቡም ቁጥጥር ይደረጋል ብለዋል። ነገር ግን ቁሶቹ የህዝቡን ጤና በማይጎዳ መንገድ ወደአገር ውስጥ በማስገባት ለኢኮኖሚያዊ ጥቅም ማዋል እንደሚቻል ገልጸው ለአብነትም የገንዲ በሽታን የሚያመጣው ዝንብን ለማምከን የተሳካ ሙከራ መደረጉን አንስተዋል። ጉባኤው ትናንት ሲጀመር የዓለም አቀፉ አቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ተጠባባቂ ዋና ዳይሬክተር ኮርኔል ፌሩታ ባስተላለፉት መልዕክት አገራት የአቶሚክ ኢነርጂን ምጣኔ ኃብታዊ እድገትን ለማምጣት ለሚያግዙ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ምርምር ሥራዎች ብቻ ለመጠቀም የገቡትን ቃል ኪዳን እንዲያከብሩ አሳስበዋል። ከጉባኤው ጎን ለጎንም ከአቶሚክ ኢነርጂ ጋር በተያያዘ የተዘጋጀው የሳይንስ መድረክም ይካሄዳል። በመድረኩ ሳይንሳዊ የምርምር ሥራዎች ይቀርባሉ ተብሏል።