ሰባተኛው የመላው ሶማሌ ክልል ስፖርታዊ ውድድር ተጀመረ

126

ጅግጅጋ /ኢዜአ/ መስከረም 6/2012 ሰባተኛው የሶማሌ ክልል የዞኖችና  ከተማ  አስተዳዳሮች  አመታዊ  የስፖርት ውድድር  ትላንት በጅግጅጋ ከተማ ተጀምሯል ።

ዓመታዊ ውድድሩ ትላንት በጅግጅጋ ስታዲየም ሲጀመር በርካታ የስፖርት ቤተሰቦች እና የክልሉ ስራ ኃላፊዎች እንዲሁም ከስድስት መቶ ሃምሳ በላይ ተወዳዳሪ ስፖርተኞች ተሳታፊ  ሆነዋል።

ከ11 ዞኖችና ስድስት የከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡት 17 ቡድኖች  በእግር ኳስ፣ በአትሌቲክስ፣ በቮሊቦል፣ በዝላይና ጠረጴዛ ቴኒስን ጨምሮ በስምንት የስፖርት አይነቶች ይሳተፋሉ።

የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኢብራሂም አብዲቃድር በመክፈቻው  ላይ እንደተናገሩት የውድድሩ ዓላማ ወጣቶችን በስፖርት ማነጽና ማቀራረብ ነው።

ከዚህ ባለፈም በውድድሩ ከሚሳተፉ ተወዳዳሪዎች መካከል የተሻሉ ስፖርተኞችን በመመልመል ክልሉን እንዲወክሉ ማድረግ እንደሆነም አስረድተዋል።

የጅግጅጋ ከተማ ከንቲባ አብዲፈታህ ሼህ ኢብራሂም ለውድድሩ ተሳታፊዎች ባስተላለፉት የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ወጣቶች ስፖርታዊ እንቅስቃሴ እንዲያድግ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ አለባቸው።

“ስፖርተኞች በውድድው ወቅት መልካም ስነ-ምግባርን በማሳየት  የክልሉ  ስፖርት  እንቅስቅሴ  እንዲያድግ የበኩላቸውን እንዲወጡ ይጠበቃል” ብለዋል።

የክልሉ ርእስ መስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሀሰን መሀመድ በበኩላቸው “ስፖርት  ጤናማ  ማህበረሰብ ለመገንባት ውሳኝ ነው”በማለት ተወዳዳሪ  ወጣቶችም  ስፖርታዊ  ጨዋነትን  እንዲላበሱ መክረዋል።

“የክልሉ መንግስት ወጣቶችን በስፖርት እና በስራ እድል ፈጠራ ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ ነው” ብለዋል።

በመክፈቻው ላይ በዶሎና  በቆረሃይ  ዞኖች መካከል  የእግር ኳስ  ውድድር  ተደርጎ  ቆረሃይ  ዞን ዶሎን ሁለት ለባዶ አሸንፏል።

ለሁለት ሳምንት በሚቆየው በዚሁ ዓመታዊ የስፖርት ውድድር ስድስት መቶ ስልሳ ሁለት ስፖርተኞች ተሳታፊ ናቸው።