ለዕውቁ የቀዶ ህክምና ሐኪም ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ መታሰቢያ ፋውንዴሽን ተቋቋመ

125
መስከረም 5/2012 ለዕውቁ ኢትዮጵያዊ የቀዶ ህክምና ሃኪም ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ መታሰቢያ በስማቸው የሚጠራ ፋውንዴሽን ተቋቋመ። ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ በእስር ቤት ቆይታቸው በህክምና፣ በሕግና በፖለቲካ ላይ የሚያጠነጥኑ ሶስት መፃሕፍት መጻፋቸውና መጻህፍቱ በወቅቱ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተወስደው መቅረታቸው ይፋ ሆኗል። 'የፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ ፋውንዴሽን' ቦርድ አባላት በተገኙበት ዛሬ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ፋውንዴሽኑ ከማንኛውም ፖለቲካዊ ወገንተኝነት የጸዳና በትምህርት፣ በጤና፣ በንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትና በሌሎች ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚሳተፍ የበጎ አድራጎት ድርጅት እንደሚሆን ታውቋል። ፕሮፌሰር አሥራት ከቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ ዘመን እስከ ኢህአዴግ መንግስት ድረስ በሃኪምነት፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ፋካሊቲ መስራችነት፣ በኃላፊነትና አስተማሪ ሆነው አገርና ህዝባቸውን ያገለገሉ ቀደምት ኢትዮጵያዊ የቀዶ ህክምና ምሁር መሆናቸውም ተወስቷል። ከአባታቸው ከአቶ ወልደየስ አልታዬና ከእናታቸው ከወይዘሮ በሠልፍይዋሉ ፅጌ በ1920 ዓ.ም በአዲስ አበባ  የተወለዱት ፕሮፌሰር አሥራት፤ እድገታቸው በድሬዳዋ ሲሆን በአብነት ትምህርት ቤት ቀለም ቀስመዋል። ገና በልጅነታቸው በቀን ከ30 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን በአንድ ቀን በግራዚያኑ በተጨፈጨፉበት ዕለት ወላጅ አባታቸውን አቶ ወልደየስን ያጡት ፕሮፌሰር አሥራት፣ ወድያውኑም እናታቸውም በሞት ሲያጡ ከአያታቸው ከቀኛዝማች ፅጌ ወረደወርቅ አማካኝነት ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ዘመናዊ ትምህርት ገብተዋል። ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀምሮ በቀለም ቀንድ እንደነበሩ የሚነገርላቸው ፕሮፌሰር አስራት፣ ግብጽ በሚገኘው የእንግሊዙ ቪክቶሪያ ኮሌጅ፣ እንዲሁም በታላቋ ብሪታንያ በሚገኘው ታዋቂው ኤደንብራ ዩኒቨርሰቲ ከመጀመሪያ እስከ ሶስተኛ ዲግሪ ተምረው ተመልሰዋል። ዛሬም ድረስ በህክምና ሙያተኞች ዘንድ ምስጋናና ከበሬታ የሚቸራቸው ፕሮፌሰር አስራት፣ በቀድሞው ልዕልት ፀሃይ  ሆስፒታል ለአምስት ዓመታት፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዛሬውን ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ወይም የጤና ሳይንስ ፋኩሊቲ በመመስራት በኃላፊነት፣ በአስተማሪነትና በሃኪምነት በአጠቃላይ ለ38 ዓመታት አገራቸውን ማገልገላቸው ተወስቷል። በሙያቸውም ከንጉሰ ነገስቱ ልዑላን ቤተሰቦች እስከ ረዳት አልባ ደሃ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ በደርግ ዘመንም ጫናው ሳይበግራቸው በበርካታ ዘመቻዎች ተልከው የጦር ቁስለኞችን በማከም ማገልገላቸውም እንዲሁ። በንጉሠ ነገሥቱ ዘመነ መንግስትም ለጤና ጥበቃ ሚኒስትርነት ታጭተው ስልጣን እንደማይፈልጉና በሙያቸው ህሙማንን መርዳት ብቻ እንደሚፈልጉ ገልጸው ኃላፊነት ሳይረከቡ መቅረታቸውም ተገልጿል። የደርግ መንግስት ከወደቀ በኋላም የኢትዮጵያ አገራዊ አንድነት እንዲጠበቅና የኤርትራን መገንጠል በመቃወማቸው በኢህአዴግ ተጽዕኖ የደረሰባቸው ሲሆን በ1985 ዓ.ም በማንነታቸው ከተባረሩ ሌሎች 42 የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዕውቅ ምሁራን መካከል አንዱ እንደነበሩም ተጠቀሷል። በወቅቱ የመንግስት ባለስልጣናት በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች በህዝቦች ላይ በተለይም በአማራ ህዝብ ላይ ግፍና በደል ሲፈጸምበት ከጎኑ የሚቆምለትና የሚወክለው ድርጅት አለመኖሩን ሲመለከቱ የ38 ዓመታት ጋውናቸውን አውልቀው የመላው አማራ ህዝብ ድርጅት/መአህድን/ መስርተው ወደ ፖለቲካው ገብተዋል። በዚህም በአማራ ህዝብ ላይ የደረሰውን በደልና ሰቆቃ በሰላማዊና በተለያዩ የተቃውሞ መንገዶች እስከ ዓለም አቀፍ ተቋማት በማስተዋወቅ ህዝባዊ ድጋፍ በማግኘታቸው ለተደጋጋሚ ጊዜ ለእስር መዳረጋቸውንም፣ ካለፍርድ ለዓመታት መታሰራቸውንና ከ150 ጊዜ በላይ ፍርድ ቤት መመላለሳቸውም ተወስቷል። በመጨረሻም ከእስር ሳይፈቱ ከዛሬ 20 ዓመት በፊት ግንቦት 6 ቀን 1991 ዓ.ም ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ በአገረ አሜሪካ ፊላደልፊያ በሚገኘው በፔንሲልቫንያ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል በህክምና ላይ እንዳሉ በ71 ዓመታቸው ነበር ያረፉት። የመቀበሪያ ስፍራ ሳይቀር በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የተነፈጉት ፕሮፌሰር አሥራት፣ በቅርቡ አፅማቸው ካረፈበት የባለወልድ ቤተክርስቲያን ወደ ቅደስት ሥላሴ በክብር አርፈዋል። በዚህም በህክምናው ዘርፍ አንቱታን የተቸሩት ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ፤ ለአገርና ለወገን ላበረከቱት አስተዋጽኦ ከ16 ዓመታት በፊት በስማቸው ፋውንዴሽን ለማቋቋም ተሞክሮ በወቅቱ የመንግስት ስርዓት ጫና ሳቢያ አለመሳካቱ ተነግሯል። በዚህም ከብዙ ጥረት በኋላ 'የፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ ፋውንዴሽን' ማቋቋም መሳካቱን የፋውዴሽኑ ስራ አስኪያጅ ፕሮፌሰር ዳዊት ሥዩም ተናግረዋል። ፕሮፌሰር አስራት የታገሉትና እስከ መስዋትነት የደረሱት ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ቢሆንም የደረሰባቸው ግፍ ግን በማንነታቸውና በፖለቲካ አቋማቸው እንደነበር ተገልጿል። ያም ሆኖ ፋውንዴሽኑ ከምንም የፖለቲካ አስተሳስብ የጸዳ፣ በመላ አገሪቱ የሚንቀሳቀሱና የሁሉም ኢትዮጵያውያን እንደሚሆንም ገልጸዋል። ተቀማጭነቱን አዲስ አበባ ያደረገው ፋውንዴሽኑ የገቢ ምንጩም ከመላው ኢትዮጵያውያን፣ አገር ውስጥም ሆነ ከውጭ ተቋማትና ከባለሀብቶች ለመሰብሰብ መታቀዱን ነው የተናገሩት። ፋውንዴሽኑ በትምህርት፣ በጤና፣ በንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትና በሌሎች ማኅበራዊ በጎ አድራጎት ስራዎች እንደሚሳተፍም አስረድተዋል። በጋዜጣዊ መግለጫው ስለፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ በቅርብ የሚያውቋቸው ግለሰቦች ምስክርነታቸውን የገለጹ ሲሆን ከነዚህም መካከል የትግል አጋራቸው የነበሩትና ከፕሮፌሰር አሥራት ጋር እስር ቤት የነበሩት ፖለቲከኛው አቶ ማሙሸት አማረ አንዱ ናቸው። ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ ሳቂታ፣ ቁጡና ደፋር ስብዕና እንደነበራቸው ገልጸው፤ ስማቸው ከገነነበት የህክምና ሙያ በተጨማሪ ጥልቅ የህግና የታሪክ ዕውቀት እንደነበራቸውም ገልጸዋል። በእስር ቤት ቆይታቸውም በህክምና፣ በህግና በወቅቱ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ሁኔታ ላይ ያተኮሩ ሶስት መጽሃፍት ጽፈው እንደነበርና በወቅቱ የመንግስት ሹመኞች ለሳንሱር በሚል ተወስዶ እንዳልተመለሰላቸው ይፋ አድርገዋል።   እስር ቤት እያሉም ከ500 በላይ ለሚሆኑ ህጻናት ወጪያቸውን እየሸፈኑ ሲያስተምሩ እንደነበር፣ ከ600 በላይ መጽሐፍትን ሰብስበውም እስር ቤት ውስጥ ቤተ መጽሐፍት ማቋቋማቸውን አቶ ማሙሸት አስታውሰዋል።   የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዝዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ በበኩላቸው የአርበኛ ልጅ በመሆናቸው፣ በልጅነታቸው በመንከራተታቸው ማኅበሩ በሚመራበት ህግ መሰረት የዲፕሎማ ማዕረግና ዕውቅና ለፕሮፌሰር አስራት እንደሚሰጥ አረጋግጠዋል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም