የዘንድሮው የሃጅ ጉዞ የክፍያ ማሻሻያ የተጓዦችን አቅም ያላገናዘበ ነው-የክልል እስልምና ጉዳይ ምክር ቤቶች

101
የዘንድሮው የሃጅ ጉዞ የክፍያ ማሻሻያ የተጓዦችን አቅም ያላገናዘበ ነው-የክልል እስልምና ጉዳይ ምክር ቤቶች አዲስ አበባ ሚያዝያ 27/2010 ለ1439ኛው የሃጅ ጉዞ የተደረገው የክፍያ ማሻሻያ የተጓዦችን አቅም ያላገናዘበ መሆኑን የክልሎች እስልምና ጉዳይ ምክር ቤቶች አስታወቁ፡፡ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በበኩሉ የዶላር ምንዛሬ መጨመርና የሳውዲ አረቢያ መንግስት ወደ ሃጂ በሚጓዙት ላይ የአምስት በመቶ ግብር ወይም ቫት መጣሉ ለክፍያው መጨመር ዋነኛ ምክንያቶች መሆናቸውን አስረድቷል። አንድ ሰው ለሀጂ ጉዞ ከአንድ ዓመት በፊት ይከፈል ከነበረው 78 ሺህ 600 ብር በያዝነው ዓመት ወደ 98 ሺህ 800 ብር ከፍ ያለ ሲሆን፤ ለአብነትም የአውሮፕላን ትኬት ክፍያ ከዓመት በፊት ከነበረበት 878 ዶላር ወደ 910 ዶላር አድጓል። የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ይህንንና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በሚመለከት ከክልሎች እስልምና ጉዳይ ምክር ቤቶች ጋር ውይይት አካሄዷል። የኦሮሚያ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ አህመድ ዛኪር አንዳሉት የክፍያ ማሻሻያ የተጓዦችን አቅም ያላገናዘበ በመሆኑ ሊስተካከል ይገባል፡፡ የትግራይ ክልል እስልምና ጉዳዮች ዋና ጸሀፊ ሃጂ ማህመድ በበኩላቸው የተደረገውን የጉዞ ክፍያ ማሻሻያ የተጋነነ በመሆኑ ምክር ቤቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተወያይቶ ችግሩን እንዲፈታ ጠይቀዋል። የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የዋጋ ጭማሪ ያደረገበትን አሳማኝ ምክንያት ለህዝበ ሙስሊሙ በግልጽ ግንዛቤ መፍጠር አለበት ብለዋል። በምክር ቤቱ ስራ አስፈጻሚና የሃጂና ኡምራ ጉዞ ሃላፊ ሼህ አህመድ የሱፍ በበኩላቸው የዶላር ምንዛሬ መጨመርና የሳውዲ አረቢያ መንግስት ወደ ሀጂ በሚጓዙት ላይ የአምስት በመቶ ቫት መጣሉ ለክፍያ ማሻሻያው ዋነኛ ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ሳውዲ አረቢያ ተጓዦች የሚያርፉባቸው የሚናና አረፋ መዳረሻዎች ላይ የአገልግሎት ክፍያ ዋጋ መጨመሯ ሌላኛው ምክንያት መሆኑንም አክለዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቀደም ሲል ለአንድ የሀጂ ተጓዥ ከጠየቀው 1 ሺህ 35 ዶላር የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት በድርድር ወደ 910 ዶላር ዝቅ ማስደረጉንም ተጠቅሰል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከዚህ በፊት የሃጅ ተጓዦችን ስነስርዓቱ ከሚካሄድበት መዲና ከተማ 400 ኪሎ ሜትር ርቀት በምትገኘው ጅዳ ያጓጉዝ እንደነበር አስታውሰው፤ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ቀጥታ ወደ መዲና በረራ እንደሚያደርግ ተናግረዋል። "ይህም የተጓዦችን እንግልትና ወጪ ይቀንሳል" ብለዋል። ኢትዮጵያ በአጠቃላይ በሳውዲ ሀጅ ሚኒስትር 43 ሺህ 337 ሰዎች ኮታ ያላት ሲሆን፤ በዘንድሮው የሃጅ ጉዞ 8ሺህ ሙስሊሞችን ወደ ሳውዲ ለማጓጓዝ ስምምነት ተደርጓል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም