ግንባታው የተቋረጠው የአምቦ-ወሊሶ መንገድ ኪሳራ እያስከተለ ነው

86
መስከረም 5/2012 ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ የኮንትራት ውል የተጀመረው የአምቦ-ወሊሶ መንገድ ግንባታ ከመቋረጡ ባሻገር አገሪቷን ለኪሳራ እየዳረጋት መሆኑ ተገለጸ። የአምቦ-ወሊሶ 64 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ የሶስት ዓመት የኮንትራት ጊዜ ተሰጥቶት ግንባታው በ2007 ዓ.ም ቢጀመርም እስካሁን እዚህ ግባ የሚባል ስራ ሳይሰራ ቆይቷል። ባለፈው ነሐሴ መጀመሪያ ኢዜአ በስፍራው ተገኝቶ ምንም አይነት ግንባታ እየተከናወነበት አለመሆኑንና ቀደም ሲል ኮንትራቱን የወሰደው የስፔን ኩባንያም ጥሎ መውጣቱን አረጋግጧል። 'ኤልሳሜክስ ኤስ.ኤ' የተሰኘው ይህ ኩባንያ ባለፈው ዓመት ለማንም ሳያሳውቅ ሰራተኞቹንና የግንባታ መሳሪያዎቹን ሜዳ ላይ በትኖ 'አካባቢውን ለቆ ወጣ' ቢባልም የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን 'ደካማ አፈጻጸም ስላሳየ ኮንትራቱን አቋርጬ ነው' ይላል። ይህን ተከትሎም የግንባታው ንዑስ ተቋራጮችና በተለያዩ የስራ ዘርፎች ተቀጥረው ሲሰሩ የነበሩ ሰራተኞች "ደሞዝ አልተከፈለንም" በማለት ክስ መስርተው ተከራካሪ በሌለበት የኩባንያውን ንብረቶች በመውሰድ ላይ ይገኛሉ። ኢዜአ ባገኘው መረጃ መሰረት ኩባንያው ሲጠቀምባቸው የነበሩት የግንባታ መሳሪያዎች ወደ አገር ውስጥ ሲገቡ መንግስት ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ከቀረጥ ነጻ ፈቅዶለታል። ሆኖም ይህ ሁኔታ ታሳቢ ሳይደረግ የወሊሶ ወረዳና የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ፍርድ ቤቶች እንዲሁም የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤትና የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔዎችን መሰረት በማድረግ ንብረቱን ግለሰቦች እየተከፋፈሉት ይገኛሉ። የወሊሶ ወረዳ ፖሊስ ኃላፊ ኮማንደር ዘውዱ ድሪብሳ እንደሚሉት መጀመሪያ ላይ ፖሊስ ለንብረቶቹ ጥበቃ ለማድረግ የተለያዩ ሙከራዎችን አድርጎ ነበር። ይሁን እንጂ ግለሰቦች ከተለያዩ ፍርድ ቤቶች የተላለፉ ውሳኔዎችና አፈጻጸሞችን እያመጡ በሕጉ መሰረት እያታጀቡ ንብረቱን ወስደውታል ነው ያሉት። ከንብረቶቹ መካከል ለተለያዩ የግንባታ ስራዎች የሚያገለግሉ ተሽከርካሪዎች፣ ኢንጂነሮች የሚንቀሳቀሱባቸው ተሽከርካሪዎችና ጄኔሬተር ይገኝበታል ተብሏል። ንብረቶቹ የተወሰዱት በፍርድ ቤቶች ውሳኔዎች መሰረት ቢሆንም ቅር የሚያሰኘው የሚመለከታቸው አካላት ቀድመው የመንግስትን ንብረት ከብክነት መታደግ እየቻሉ ይህን አለማድረጋቸው ነው ይላሉ ኮማንደሩ። የወሊሶ ወረዳ ፍርድ ቤት' ፕሬዚዳንት አቶ ቦጋለ ፉፋ 'ሰዎች ክስ ይዘው መጥተው ሕጉ በሚፈቅደው መሰረት ውሳኔ ተሰጥቷቸዋል' ብለዋል። በአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ መሰረት ተከሳሹ ከአንድም ሁለት ጊዜ መጥሪያ ተልኮለት ባለመገኘቱ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ መስጠቱንም ገልጸዋል። አቶ ቦጋለ ፍርድ ቤቱ እስከሚያውቀው ድረስ በኩባንያው ተመዝግቦ የሚገኘው ንብረት የኩባንያው የግል ንብረት ስለሆነ በዛ መሰረት ውሳኔ ተሰጥቷል ባይ ናቸው። ይሁን እንጂ ሌሎች ጉዳዮች በፍርድ ቤት በኩል ያለፉ ቢሆንም የወሊሶ ወረዳ ገቢዎች ቢሮ ደግሞ ያለፍርድ ቤት ውሳኔ በኩባንያው የተመዘገቡ ተሽከርካሪዎችን ወስዶ ለብክነት ዳርጓል ሲሉ ይወቅሳሉ። የወሊሶ ወረዳ ገቢዎች ቢሮ በበኩሉ ኩባንያው 46 ሚሊዮን ብር ያልከፈለው ገንዘብ ስላለ የገቢዎችና ጉምሩክ አዋጅ በሚፈቅደው መሰረት ቢሮው 'ተሽከርካሪዎቹን ወስዷል' ይላሉ። ኩባንያው የሚፈለግበትን ከሰራተኞች ደሞዝ ላይ የተቆረጠ 32 ሚሊዮን ብር ገቢ ግብርና 14 ሚሊዮን ብር የጡረታ መዋጮ ሰብስቦ ባለማስገባቱ በኩባንያው የተመዘገቡ 50 ተሽከርካሪዎችን ቢያሳግድም ማግኘት የቻለው ሰባት ብቻ ነው ብለዋል። የቢሮው ኃላፊ አቶ ሙሉዓለም በድሉ ደግሞ ሰራተኞች ናቸው ተብለው የኩባንያውን ንብረቶች በፍርድ ቤት ውሳኔ እየወሰዱ ያሉት ግለሰቦች 'ማጣራት ሳይደረግባቸው ነው ንብረቱን የወሰዱት' ይላሉ። የወረዳው ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ቦጋለ ይህ ትክክል አለመሆኑንና ፍርድ ቤቱ ትክክለኛውን ሂደት ጠብቆና የሰራተኞቹን የቅጥር ሁኔታ አጣርቶ ውሳኔ መስጠቱን ተናግረዋል። የገቢዎች ቢሮ ኃላፊው ተሽከርካሪዎቹ ለተጨማሪ ብልሽት እንዳይዳረጉ ጨረታ አውጥቶ ለመሸጥ ቢታሰብም አሁንም ተጨማሪ ክሶች ወደ ፍርድ ቤት እየመጡ የጨረታውን ሂደት እያስተጓጎሉ እንደሆነ ገልጸዋል። የፕሮጀክቱ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን በበኩሉ የተለያዩ ምክንያቶችን ከማቅረብ ውጭ ቀርቦ ዝርዝር ማብራሪያ መስጠት አልፈለገም። ባለስልጣኑ አንዴ "የሚመለከተኝ የኮንትራት ሂደቱን መከታተል ነው እንጂ የኩባንያው ንብረት ጉዳይ አይደለም" ሌላ ጊዜ "ባለስልጣኑ በዚህ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ የሚሰጥበት ምንም ጉዳይ የለውም" በማለት ምላሽ ሰጥቷል። የኮንትራት ውል ሲቋረጥ እንደ አገር ኪሳራ ማጋጠሙ የማይቀር ቢሆንም ባለስልጣኑ ምን ያህል ኪሳራ እንዳጋጠመው ማወቅ አልተቻለም። ባለስልጣኑ ለሁሉም ፕሮጀክቶቹ አማካሪዎችን መድቦ የኮንትራት አስተዳደር ስራውን በቅርበት እንደሚሰራ የኮንትራት አስተዳደር መመሪያው ያትታል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም