በአንድ ባለሃብት የተገነባ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመርቆ ለአገልግሎት ተዘጋጀ

60
መስከረም 5/2012 በዋግህምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ሰቆጣ ወረዳ በአንድ በጎ ፈቃደኛ ባለሃብት በ7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባ አንድ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመርቆ ለአገልግሎት ተዘጋጀ። በአፍሮ ጽዮን ኮንስትራክሽን ወጪ ይኸው ትምህርት ቤት ተገንብቶ ለአገልግሎት የተዘጋጀው በዋግ ልማት ማህበር በ2006 ዓ.ም በተካሄደው የገቢ ማሰባሰቢያ ቴሌቶን ቃል በገቡት መሰረት ነው። ትምህርት ቤቱ 8 የመማሪያ ክፍሎች፣ ቤተ መጻህፍትና የመምህራን ማረፊያ እንዲሁም ለ150 የተማሪዎች መቀመጫ ወንበር ጭምር የተሟላለት መሆኑን የኮንስትራክሽኑ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሲሳይ ደስታ ገልፀዋል። በትምህርት ተደራሽነት ችግር ምክንያት በርካታ ህፃናት ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆናቸውን በመመልከት ትምህርት ቤቱን ለመገንባት መነሳሳታቸውን ገልፀዋል። በቀጣይም በትምህርት ዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮች እስኪፈቱ ከመንግስት ጎን በመሆን አቅማቸው በፈቀደ መጠን ድጋፍና እገዛ እንደሚደርጉ አስታውቀዋል። የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ይልቃል ከፍአለ በበኩላቸው ትምህርት የልማት ሁሉ መጀመሪያ በመሆኑ የሚመለከተው አካል ተገቢውን ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ የመንግስትን የአቅም ክፍተት በመሙላትም ባለሃብቶች የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሌሎች ባለሃብቶችም በተደራጀ አግባብ ሊደግፉ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ በተለይም ''የዳስ ጥላ ስር ትምህርት ቤቶችን ሙሉ በሙሉ ወደ ክፍል ለመቀየር እየተደረገ ባለው የመንግስት ጥረት ባለሃብቶች ጉልህ ሚና ሊጫዎቱ ይገባል'' ብለዋል። የዋግ ልማት ማህበር ዋና ዳይሬክተር አቶ ባምላክ አበበ በበኩላቸው ማህበሩ የብሄረሰብ አስተዳደር ዞኑን ህዝብ ማህበራዊና ኢኮኖሞዊ ጠቀሜታ ለማሳደግ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡ በ2006 ዓ.ም በተካሄደው የገቢ ማሰባሰቢያ ቴሌቶን ከተገኘው 500 ሚሊዮን ብር ውስጥም ግማሹ ለትምህርት ስራ መዋሉን አስታውቀዋል። አፍሮ ጽዮን ኮንስትራክሽን ያደረገው ድጋፍም የበጎነት ማሳያና ማስተማሪያ ነው ብለዋል። የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር አቶ ገብረማርያም ጌጡ በበኩላቸው ቀደም ሲል ትምህት ቤቱ ደረጃውን ባልጠበቀ ሁኔታ በዳስ ውስጥ ተማሪዎችን ሲያስተምር መቆየቱን ጠቅሰዋል። በዚህም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎች በየዓመቱ ትምህርት ያቋርጡ እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ላይ ትምህርት ቤቱ ደረጃውን ጠበቆ መገንባቱ ለመማር ማስተማር ስራው መሳለጥ ከፍተኛ እገዛ እንደሚኖረው ገልፀዋል፡፡ የትምህርት ቤቱ ግንባታ ተጠናቆ ለአገልግሎት በመዘጋጀቱም ከዚህ በፊት ከ1 እስከ 4ኛ ክፍል ይሰጥ የነበረው ትምህርት እስከ 8ኛ ክፍል ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር እንደሚያስችለው ተናግረዋል። ትምህርት ቤቱም በባለሃብቱ አቶ ሲሳይ ደስታ ስም እንዲሰየም መወሰኑ ታውቋል፡፡ በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይም በየደረጀው ያሉ አመራሮች፣ መምህራንና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል። በክልሉ የሚገኙ የዳስ ትምህርት ቤቶችን ወደ ህንፃ ለመቀየር በሚደረገው ጥረት የክልሉ ተወላጅ ባለሃብቶች 12 ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት ተሰማምተው ወደ ስራ መግባታቸው ታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም