በምሁራን ተጠንቶ የቀረበው የትግራይ ክልል የቱሪዝም ልማት ሰነድ ተግባራዊ ሊደረግ ነው

72
መቀሌ ኢዜአ መስከረም 4/2012-በምሁራን ተጠንቶ የቀረበው የትግራይ ክልል የቱሪዝም ልማት ሰነድ በቅርቡ ተግባራዊ እንደሚደረግ ተገለጸ። ሰነዱ በክልሉ በተመረጡ አራት የቱሪዝም መስህብ ስፍራዎች በሙከራ ደረጃ እስከመጪው ህዳር ወር ድረስ ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት ተደርጓል። በመቀሌ ከተማ ትናንት በሰነዱ አፈጻጸም ዙሪያ የውይይት መድረክ ተካሄዷል። በዋናነት ሰነዱ በየአካባቢው የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ከዘርፉ መጠቀም እንዲችሉ ተጠንቶ የቀረበ መሆኑን የጥናቱ ዋና አሰተባባሪ ዶክተር ሙሉጌታ ፍሰሃ ተናግረዋል። በክልሉ የሚገኙ አራት ዩኒቨርሲቲዎች፣ የክልሉ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣ በመስህብ ስፍራዎች የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎችና ባለሃብቶች በቅንጅት እንዲሰሩ ሰነዱ መመቻቸቱን አመልክተዋል። ዶክተር ሙሉጌታ እንዳሉት ሰነዱ በውጭና በሃገር ውስጥ በሚገኙ የክልሉ ተወላጅ ምሁራን ባደረጉት ጥናት በተለይ በቱሪዝም ልማት ዘርፍ የሚታዩትን ችግሮችን በዝርዝር በመዳሰስ መፍትሄዎችን የቀየሰ ነው። ሰነዱ በክልሉ ያሉትን እምቅ የቱሪዝም መስህብ ስፍራዎችና ቅርሶችን ለዘርፉ ልማት በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ናየህብረተሰቡም ተጠቃሚነት የሚያረጋገጥበት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑን አመልክተዋል፡፡ የመስህብ ስፍራዎችን በመሰረተ ልማት የማልማት፣በሚገባ የማስተዋወቅና ሌሎችም ተጓዳኝ ስራዎች የሚውልበት እድል በሰነዱ ተካቷል። በሙከራ ደረጃ በተመረጡ አራት መስህብ ስፍራዎች በቅርቡ ተግባራዊ ይደረጋሉ ተብሏል። ይህም በመቀሌና አክሱም እንዲሁም በገርዓልታ ሰንሰለታማ ተራሮችና በሐሸንገ ሃይቅና አካባቢው እስከ ህዳር 2012 ዓ.ም ድረስ ተግባራዊ እንደሚደረግ ተገልጿል። በአራቱ አከባቢዎች ስራ ላይ የሚውለው የክልሉ የቱሪዝም ልማት ሰነድ ውጤታማነቱ ታይቶ በሌሎች የክልሉ የመስህብ ስፍራዎች እንደሚስፋፋ የተናገሩት ደግሞ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ብርክቲ ገብረመድህን ናቸው። ሰነዱ በተለይ የምሁራን እውቀት፣ክህሎትና  ልምድ ያረፈበት በመሆኑ ለክልሉ ቱሪዝም ልማት ዘርፍ ስኬት ትልቅ ግብአት መሆኑን ገልጸዋል። የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረ ህይወት በበኩላቸው፣ሰነዱ የክልሉን የቱሪዝም ልማት ወደ ላቀ ደረጃ ትራንስፎርም ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አስረድተዋል። ሰነዱን ወደ ተግባር ለመቀየር የማስተዋወቅ ስራው ትኩረት መስጠት እንደሚገባ አመልክተው "በተለይ በየትምህርት ቤቱ ስራው መጀመር አለበት፤ ሌሎች አካላትም በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል" ብለዋል። የአክሱም ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ጸሃዬ አስመላሽ እንዳሉት ፣ሰነዱን ለመተግበር የሚመለከታቸው አካላት በቅንጅት መስራት ይጠበቅባቸዋል፤ ተቋማቸውም ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነው። በውይይት መድረኩ ማጠቃላያ ላይ በሰነድ ጥናቱ ላይ የላቀ ተሳትፎ ላደረጉ ምሁራን የእውቅና የምስክር ወረቀት ሰተጥቷቸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም