በትግራይና አፋር ሁለት አጎራባች ቀበሌዎች የሚያገናኝ መንገድ ለመስራት የሚያግዝ የገቢ ማሰባሰቢያ ቴሌቶን ተካሄደ

76
መቀሌ መስከረም 4/2012 በትግራይ ሓድሽ ዓዲ እና በአፋር ዓሳጋራ ቀበሌዎች የሚያገናኝ የአምስት ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ ለመስራት የአካባቢው ተወላጆች ያዘጋጁት የገቢ ማሰባሰቢያ ቴሌቶን ተካሄደ። ቴሌቶኑ“እናት ህይወት እየሰጠች ህይወቷ ማጣት የለባትም” በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ በመቀሌ ከተማ  ተካሂደዋል። የሁለቱም ክልሎች አጎራባች አካባቢዎችን በመንገድ ለማስተሳሰር እንዲያግዝ የገቢ ማሰባሰቢያ ቴሌቶኑን ያዘጋጁት የሁለቱም ቀበሌ  ተወላጆች ናቸው። መንገዱ አጭር ርቀት ያለው ቢሆንም ገደላማና ተራራማ የበዛበት በመሆኑ በሰው ጉልበት ለመገንባት አስቸጋሪ ነው። የገቢው አሰባሳቢው ኮሚቴ አስተባባሪ አቶ መሓሪ ንጉስ እንዳሉት የመንገዱ መገንባት  ለሁለቱም ህዝቦች ልማትና ማህበራዊ ግንኙነት እንዲጠናከር ያግዛል። በመንገድ ችግር ምክንያት በወልድ  ምክንያት ህይወታቸው እያጡ ያሉ እናቶች ለመታደግ እንዲያግዝ የተጀመረው  የገቢ ማሰባበሰቢያ ቴሌቶን ቀጣይነት እንዳለውም ተመልክቷል። ለሁሉም ችግሮች የመንግስት እጅ ከመጠበቅ ይልቅ የአካባቢው ተወላጆች   በመደጋገፍ መንገዱን ለመስራት መነሳሳታቸውን  አቶ መሓሪ ተናግረዋል። "መንገዱን ለመገንባት 5 ሚሊዮን ብር ያስፈልጋል "ያሉት አቶ መሓሪ ከቴሌቶኑ 2 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ዛሬ  ከ800ሺህ ብር በላይ  ድጋፍ መገኘቱን አስታውቀዋል። በቴሌቶኑ 5ሺህ ብር ያበረከቱት የአፋር ተወላጅ ሓጂ ዓሊ ሑሴን መሐመድ  በሰጡት አስተያየት" መንገዱ የሁለቱ ህዝብ ማህበራዊ ትስስር እንዳይጠናከር እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል "ብለዋል። መንገድ ተሰርቶ እስኪያልቅ ድጋፋቸው አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል። በመንገድ ችግር እናቶች በቤታቸው ለመውለድ በመገደድ ህይወታቸው እያጡ መሆኑን  የተናገሩት ደግሞ በትግራይ የሳእስዕ ጻእዳ አምባ ወረዳ የሓዱሽ ዓዲ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ለተብርሃን ኪሮስ ናቸው ። ሰድዋ ሓዊለ /ዓቐብ ዳዕሮ/ መንገድ ከ1968 እስከ 2009 ዓ.ም በየዓመቱ በሰው ጉልበት ለመስራት ሙከራ ቢደረግም  እስካሁን ተሽከሪካሪ መግባት አለመቻሉም ተመልክቷል። መንገዱ የሚሰራው በትግራይ ክልል ሳዕስዕ ፃዕዳእምባ ወረዳ ሓድሽ የዓዲ እና በአፋር ክልል ዳሉል ወረዳ ዓሳጋራ ቀበሌዎች ለማገናኘት ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም