"የተማረ ትውልድ ምን ጊዜም አሸናፊ ነው" - የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ

116
አዲስ አበባ ኢዜአ መስከረም 4/2012 " በሁሉም የትምህርት እርከን የምትገኙ ተማሪዎች ለወደፊት ህይወታችሁ አቅጣጫ መተለሚያ ለሆነው የትምህርታችሁ መጀመሪያ ቀን እንኳን አደረሳችሁ" ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ። ምክትል ፕሬዝዳንቱ ነገ የሚጀመረውን የ2012 ዓ.ም የትምህርት ዘመን አስመልክተው ለተማሪዎች "የእንኳን አደረሳችሁ" መልእክት አስተላልፈዋል። አቶ ሽመልስ በዚሁ መልዕክታቸው እንደጠቀሱት፤ በመላው አገሪቷ አሁን ለተጀመሩ የለውጥ ጎዞዎች ከጀርባው ያለው ምስጢር ትምህርት ነው። በዚህም "የተማረ ትውልድ ምን ጊዜም አሸናፊ ነው" ያሉት አቶ ሽመልስ፤ በታላቅ ስነ ምግባር፣ በህብረትና በስትራቴጂ ተመርተውና ግንባራቸውን ለጥይት ሰጥተው ወደ አዲስ ምዕራፍ በድል ያሻገሩ ወጣቶችን ማስታወስ የሚቻለው በርትቶ በመማር መሆኑን ጠቁመዋል። አሁን ያለው አሸናፊ ትውልድ የማይቻል የሚመስለውን በመቻል "ለውጥ አምጥቷል" ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፤ ትምህርት የእነርሱ ተጋድሎ የሚዘከርበትና ለውጡን ለማሻገር የሚያስችል አቅም መሆኑን ገልጸዋል። በተለይም እንደነጄኔራል ታደሰ ብሩ ያሉ አባቶች "ትውልዱ ይማር፤ የተማረ ሰው መብቱን ይጠይቃል" ማለታቸውን በመልዕክታቸው አስታውሰው፤ የኦሮሞ ህዝብ የሚያካሂደው ትግል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ መጥቶ አሁን ለተገኘው የለውጥ ደረጃ ለመብቃት ትምህርት ከፍተኛ ሚና ለመጫወቱ ማሳያ መሆኑን አመላክተዋል። በተለይም ትምህርት ለኦሮሞ ህዝብ "በራሱ ትግል ነው፣ ድል ነው፣ በትምህርት ታግዞ ማንኛውንም ችግር የማለፍ ጉዳይ ነው፣ በአንድነት ተባብሮ ማንኛውንም ችግር መሻገርም ነው" በማለት የትምህርትን አስፈላጊነት አጽንኦት ሰጠውታል። ለበለጠ ድል ለመብቃትና ተወዳዳሪ ለመሆን መማር ግዴታ መሆኑን ያወሱት ምክትል ፕሬዝዳንቱ፤ በለውጥ ጉዞ ጥቃቅን ነገሮች ከግብ ማስተጓጎል እንደሌለበት በመልክታቸው ገልጸዋል። በትምህርት መሳሪያነት የወጣቱን አደራ ከዳር ለማድረስ እንደሚሞከርም ነው የጠቆሙት። አቶ ሽመልስ እንደገለጹት፤ ትምህርት ቤቶች ሰላምን በማስጠበቅና በመጠበቅ፣ ለእውቀት የተዘጋጀና ብቁ፣ በዓለም ተወዳዳሪ የሆነ ትውልድ ለመፍጠር መስራት ይኖርባቸዋል። ድልን በትምህርት በማጠናከር ዓላማን ከግብ ማድረስ ያስፈልጋል። "ተማሪዎቻችን ሙሉ ጊዜያችሁን ለትምህርት ማዋል ይኖርባችኋል፤ በአንድነት በማጥናትም በመደጋገፍ ለላቀ ደረጃ መድረስ አለባችሁ። በትምህርት አሸናፊ በመሆን በአሳብ ለማሸነፍ መትጋት ይኖርባችኋል" ብለዋል። መምህራን "የትውልድ አረዓያ ናችሁ በዚህም ክብርና ምስጋና ይገባችኋል" ያሉት ምክትል ፕሬዝዳንቱ፤ በአዲሱ ዓመት በመሰናክሎችና ችግሮች ሳይታጠሩ አዲስ ትውልድ ለመቅረጽ ተግተው እንዲሰሩ አስገንዝበዋል። በተጨማሪም በተማሪዎች መካከል የውድድርና የመማር መንፈስ እንዲያድግ ባላቸው ጊዜ ሁሉ የነገን ትውልድ ለመቅረጽና የትምህርትን ጥራትን ለማረጋገጥ የሚሰሩበት እንዲሆን ተመኝተዋል። በክልሉ በሚገኙ ቀበሌዎች በሙሉ ትምህር ቤት በመገንባት የትምህርትን ተደራሽነት ለማስፋት ህዝቡ የሚጠበቅበትን ሁሉ ሲያከናውን መቆየቱን አውስተዋል። በዜግነት አገልግሎት መርሃ ግብርም ተጨማሪ ክፍሎችን የመገንባት ስራ፣ ትምህርት ቤቶችን የማደስና አዳዲስ ትምህርት ቤቶችን የመገንባት ተግባራት መከናወኑን አስታውሰው፤ በዚህም የመተጋገዝ፣ የመተባበርና ችግርን በራስ የመወጣት ባህል በተጨባጭ መታየቱን ጠቁመዋል። ለዚህም "ምስጋና እያቀረብኩ ለወደፊቱም ተጠናክሮ እንዲቀጥል አደራ እላለሁ" በማለት አጽንኦት ሰጠውታል። የሁላችን ዓላማ "በራሱ የሚተማመን፣ ባህልና ወጉን ጠንቅቆ በማወቅ አገሩን የሚገነባ ትውልድ መፍጠር ነው" ያሉት አቶ ሽመልስ፤ ለሁሉም የምትበቃና የለማች አገር መገንባት ትልቁ ግብ መሆኑን አብራርተዋል። በውይይትና በምክክር ችግሮችን የመፍታት፣ ሌት ተቀን የመስራትና በሁሉም መስክ ተወዳዳሪነት ያለውና አሸናፊ ትውልድ የመፍጠር የቆየ እሴትን ለማሳደግ በእውቀትና በትብብር መንፈስ መስራት ያስፈልጋል። "ዛሬ ላይ ሆነን የምንሰራው ስራ የነገው ውጤት ያማረ እንዲሆን ያስችላል" ያሉት አቶ ሽመልስ፤ ትምህርት አሸናፊ ትውልድን ለበለጠ ድል የሚያበቃ መሳሪያ መሆኑን ገልጸዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም