ዩኒቨርሲቲው በመሬት አጠቃቀም የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት በምርምር ታግዞ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ

165
መስከረም 4/2012 በኢትዮጵያ መሬት አስተዳደር፣ አያያዝና አቃቀም የሚስተዋሉ መሰረታዊ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት በምርምር ታግዞ እየሰራ መሆኑን በባህርዳር ዩንቨርሲቲ የመሬት አስተዳደር ተቋም አስታወቀ። የተቋሙ ዲን ዶክተር በላቸው ይርሳው ለኢዜአ እንዳሉት ስራው ከመሬት ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ የአሰራር ክፍተቶችን በእውቀት ላይ ተመስርቶ በመለየት መፍትሄ እንዲያገኙ ለማስቻል ነው። ለዚህም ተቋሙ የአጭር፣ የመካከኛና የረጅም ጊዜ እቅድ መያዙን አመልክተው ለስራ መሳካት ከሚያግዙ ከስዊድን አለም አቀፍ ድርጅትና ሌላም ባለድርሻ ጋር በትብብር እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል የኢትዮጵያ መሬት አያያዝና አጠቃቀም ኋላ ቀርና በሳይንሳዊ አሰራር ያልተደገፈ በመሆኑ በየአባቢው ለመልካም አስተዳደር መጓደል አንዱ ምክንያት እንደሆነ አመልክተዋል። ለዘመናት የቆየው ይህንን  ችግር  በዘላቂነት እንዲፈታ የሰው ኃይል የማሰልጠንና  ዘመናዊ የአሰራር ስርዓት እንዲዘረጋ የሚያግዙ የመፍትሄ ሃሳቦችን ጥልቀት ባለው ጥናት በመለየት  እልባት እንዲያገኝ ለማስቻል እየተሰራ ነው። ዶክተር በላቸው እንደተናገሩት የሰው ኃይል ክፍተቱን ለመሙላትም ባለፉት ስድስት ዓመታት በመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ ፕሮግራሞች አንድ ሺህ 617 ተማሪዎችን አሰልጥነው ወደ ስራ እንዲገቡ ተደርጓል። እንደተቋሙ ዲን ገለጻ የዳበረ ልምድ ካላቸው ሃገሮች ቴክኖሎጂዎችን ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት የዘርፉ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኙ ትኩረት ተሰጥቷል። ተቋሙ የምስራቅ አፍሪካ የመሬት አስተዳደር ትስስር ከሚባል ድርጅት ጋር አባል በመሆንም በዘርፉ አለም የደረሰበትን እውቀት፣ ቴክኖሎጂና የሰለጠነ አሰራር ለሀገሪቱ በማምጣት ውጤታማ ስራ እየተከናወነ ነው። በቀጣይም ደረጃውን የጠበቀ የየልህቀት ማዕከል ለማሟላት የራሱ የስልጠና ማዕከል፣ የቪዲዮ ኮንፍረንስና ምርምር ላይ  በማተኮር እንደሚሰራ አብራርተዋል። ተቋሙ በሀገሪቱ ያለውን የመሬት አያያዝና አስተዳደር ክፍተት ለመሙላት ትኩረት አድርጎ በመስራት ለውጥ እንዲመጣ የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የተቋሙ መምህርና ተመራማሪ አቶ አመዘነ ረዳ ናቸው። የተማሪዎችንና የስራ ላይ ሰልጣኞችን አቅምና ክህሎት ለማሳደግ በኮምፒዩተርና ሌሎች መሳሪዎች የተሟሉ አምስት ቤተሙከራዎች ከሚያስተምሩ 67 ምሁራ ጋር መሟላታቸውን ጠቅሰዋል። በመስክና ቤተሙከራ የተደገፈ ተግባር ተኮር የትምህርት አሰጣጥ ዘዴ በመተግበሩም ተመራቂዎች ያለምንም ተጨማሪ ስልጠና ፈጥነው ወደ ስራ በመግባት በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት እያገዙ እንደሚገኝ በጥናት ማረጋገጣቸውንም አስታውቀዋል። በተቋሙ የመሬት አስተዳደርና የቅየሳ መምህርና ተመራማሪ አቶ ዝናቡ ጌታሁን በበኩላቸው ተቋሙ  በሀገሪቱ የመጀመሪያ በመሆኑም በቅርቡ የመሬት አስተዳደር ማስተማር ለጀመሩ ዩንቨርሲቲዎች እገዛ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ከሳተ ላይት የመሬት መረጃ የሚቀበል ቴክኖሎጂን በመትከል፣ ዘመናዊ የቅየሳና ሌሎች መሳሪያዎችን በማስገባት ለምርምርና ለመማር ማስተማር ስራ እያዋሉ ናቸው። እንደ አቶ ዝናቡ ገለጻ በተለይም በምርምርና ማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት በኢትዮጵያ የሚገኙ የ53 ከተሞችን የአየር ላይ ፎቶ ግራፍ ከመሬት ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማጣጣም የካርታ ዝግጅትን ለመስራት መሳሪያዎቹ ጉልህ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ። ተቋሙ በተያዘው ዓመትም በመጀመሪያ፣ ሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪ ፕሮግራሞች ከ200 በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ ስልጠና ለመጀመር እየተዘጋጀ መሆኑም ተመልክቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም