ጥያቄዎች አሉን የሚሉ አካላት ሃሳባቸውን በትዕግስትና በሰከነ መንገድ ማቅረብ አለባቸው - ጠ/ሚ አብይ አህመድ

አዲስ አበባ መስከረም 4/2012 ማናቸውም አይነት ጥያቄዎች አሉን የሚሉ አካላት ሃሳባቸውን በትዕግስትና በሰከነ መንገድ ማቅረብ እንዳለባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አሳሰቡ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተለያዩ የኀብረተሰብ ክፍሎች ከተውጣጡ የከፋ ዞን ቦንጋ ከተማ ነዋሪዎች ጋር ተወያይተዋል። የከተማዋ ነዋሪዎች በዋናነት የመንገድ፣ የውሃ፣ የሕክምና ግብዓትና ሌሎች መሰረተ ልማቶች አቅርቦት እንዲሁም የክልል አደረጃጀት ጥያቄዎችን አንስተዋል። በተለይም የቦንጋ ከተማ ከክልሉ ርዕስ መዲና ሃዋሳ ጋር ያለው ርቀት ረጅም  በመሆኑ ለእንግልት እየተዳረጉ መሆናቸውን አንስተው ዞኑ ራሱን ችሎ በክልል እንዲደራጅ ጠይቀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በበኩላቸው መንግስት በዘንድሮ በጀት ዓመት መንገድን ጨምሮ ለመሰረተ ልማት ግንባታ ትልቅ ትኩረት መስጠቱን አንስተዋል። መንግስታቸው በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ የተነሳው የመሰረተ ልማት ችግር ለማቃለል እንደሚሰራም ተናግረዋል። የክልል አደረጃጀትን በሚመለከት የዞኑ ሕዝብ በሰከነና ጥናትን መሰረት ባደረገ መልኩ ከክልሉ ምክር ቤት ጋር ተቀራርቦ በጉዳዩ ላይ ከመግባባት ሊደርስ እንደሚገባም መክረዋል። የከፋም ሕዝብ ሆነ ሌሎች ጥያቄ አለን የሚሉ አካላት ሃሳባቸውን ከስሜታዊነት በፀዳና በሰከነ መንገድ ማቅረብ እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም