ለሁሉም ክፍት የሆነ የወርልድ ቴኳንዶ ውድድር ከመስከረም 7 ጀምሮ ይካሄዳል

107
አዲስ አበባ መስከረም 4/2012 ለሁሉም ክፍት የሆነ የወርልድ ቴኳንዶ ውድድር ከመስከረም 7 እስከ 9 ቀን 2012 ዓ.ም ይካሄዳል። በቦሌ ከፍለ ከተማ ወረዳ 17/18 የወጣት ማዕከል በሚካሄደው ይኸው ውድድር ከዘጠኙ ክልሎች እና ከሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ 300 ተወዳዳሪዎች ይሳተፉበታል ተብሎ ይጠበቃል። በሴት ከ49፣ 57 እና 67 ኪሎ ግራም በታች እንዲሁም በወንድ ከ58፣ 60 እና 80 ኪሎ ግራም በታች ውድድሩ የሚካሄድባቸው የክብደት ዘርፎች ናቸው። የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ፍቅሩ ተቋም ለኢዜአ እንደገለጹት በውድድሩ ላይ ጥሩ ብቃት የሚያሳዩ ተወዳዳሪዎች ለ2020ው የቶኪዮ ኦሎምፒክ እንዲሁም በጥር 2012 ዓ.ም በሞሮኮ በሚካሄደው ማጣሪያ ኢትዮጵያን ወክሎ ተሳታፊ የሚሆነው ብሔራዊ ቡድን ጋር ይቀላቀላሉ። በሴት አምስት በወንድ አምስት ስፖርተኞች ከውድድሩ ላይ እንደሚመረጡና የተመረጡት ተወዳዳሪዎች በአሁኑ ሰአት በወርልድ ቴኳንዶ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ካሉ ስድስት ስፖርተኞች ጋር ልምምድ ማድረግ እንደሚጀምሩም ተናግረዋል። በሞሮኮ በሚካሄደው የቶኪዮ ኦሊምፒክ የማጣሪያ ውድድር በሴት ሁለት በወንድ ሁለት በድምሩ አራት ስፖርተኞች እንደሚሳተፉም ገልጸዋል። ውድድሩ ለሁሉም ከፍት በመሆኑ ለወርልድ ቴኳንዶ ስፖርት ተወዳዳሪዎች የውድድር አማራጭ የሚፈጥር እንዲሁም አቋማቸውን የሚፈትሹበትና ልምድ የሚያገኙበት እንደሆነም አመልክተዋል። ለሁሉም ክፍት የሆነው የወርልድ ቴኳንዶ ውድድር ማንኛውንም ተወዳዳሪ የሚያሳትፍ በመሆኑ የተሳታፊዎች ቁጥር ከተባለው በላይ ሊጨምር እንደሚችልም ገልጸዋል። በሌላ በኩል ነገና ከነገ በስቲያ ቦሌ የብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ጽህፈት ቤት በሚገኘው የወርልድ ቴኳንዶ ጂምናዚየም የባለሙያዎች የዳን የደረጃ ማሻሻያ ፈተና እንደሚሰጥም የፌዴሬሽኑ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ገልጸዋል። በፈተናው ከ1ኛ እስከ 5ኛ ዳን እንደሚሰጥና ከሰባት ክልሎችና ከሁለት ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የወርልድ ቴኳንዶ 300 ተወዳዳሪዎችና አሰልጣኞች ይሰጣል ተብሎም ይጠበቃል። ፈተናውን አምስተኛና ስድስተኛ ዳን ያላቸው ስምንት ባለሙያዎች እንደሚሰጡና ለአሰልጣኞችና ተወዳዳሪዎች የንድፈ ሀሳብና የተግባር ፈተና እንደሚሰጣቸውም ተናግረዋል። የኦሮሚያና የአማራ ክልሎች ከዚህ አሰልጣኝ ተልኮላቸው ለባለሙያዎች የዳን የደረጃ ማሻሻያ ፈተና እንዲሰጥ ጥያቄ አቅርበዋል። ባለፈው ዓመት ፌዴሬሽኑ ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ በወሰነው መሰረት በክልሎች የዳን ፈተና የሚሰጠው ክልሎቹ ከ100 በላይ ሰልጣኞችን የሚያስፈትኑ ከሆነ እንደሆነ ገልጸው በዚሁ መሰረት ሁለቱ ክልሎች የተባለውን መስፈርት ማሟላታቸውን ገልጸዋል። ፈተናው በኦሮሚያ ክልል መስከረም 10 እና 11 ቀን 2012 ዓ.ም በአማራ ክልል ደግሞ መስከረም 20 እና 21 ቀን 2012 ዓ.ም  ይሰጣል። በአጠቃላይ የዳን የደረጃ ማሻሻያ ፈተናውን ያለፉ ተወዳዳሪዎች የስም ዝርዝራቸው በመስከረም መጨረሻ ለዓለም አቀፉ የወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን እንደሚላክም ነው አቶ ፍቅሩ የጠቆሙት። የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን በተያዘው በጀት ዓመት የዳኝነትና የአሰልጣኝነት ስልጠናዎችን በስፋት በመስጠት የሙያተኞችን አቅም ማጎልበት ላይ ዋነኛ ትኩረቱን አድርጎ እንደሚሰራም አመልክተዋል። ከፍተኛ ክፍተት ያለበት የታዳጊ ፕሮጀክት ክትትልና ድጋፍን ማጠናከር፣ የወርልድ ቴኳንዶ ክለቦች እንዲቋቋሙ ማድረግና ክልሎች የራሳቸውን ውድድር እንዲያዘጋጁ ማድረግ ሌሎች የሚከናወኑ ተግባራት ናቸውም ብለዋል። መከላከያ የራሱን ክለብ ለማቋቋም እንደሚፈልግ መግለጹንና የአማራ፣ የኦሮሚያና የደቡብ ክልሎችም የየራሳቸውን  ለማቋቋም ፍላጎት እንዳላቸውም ጠቁመው ከውድድሩ አንጻርም የአዲስ አበባ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን የራሱን ውድድር ለማዘጋጀት እንደሚፈልግም ገልጸዋል። የኮሪያ የባህል ስፖርት በሚል የሚታወቀው ወርልድ ቴኳንዶ ከሰውነት ፍልሚያ ባሻገር ጥበባዊ ስልቶችን ያካተተ ክንዋኔ ሲሆን አእምሮና ሰውነት ማሰልጠንን ጨምሮ ህይወትን በአግባቡ ለመምራት የሚያግዝ የስፖርት ዓይነት እንደሆነም የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ። የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን በ1995 ዓ.ም በብሔራዊ ደረጃ የተቋቋመ ሲሆን ስፖርቱ ከአትሌቲክስ በመቀጠል በዓለም አቀፍና በአህጉር ደረጃ ውጤት በማስገኘት አገሪቷን በማስጠራት ላይ ይገኛል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም