የጤና መድህን በቀላሉ የህክምና አገልግሎት ማግኘት እንዳስቻላቸው በጉርሱም ወረዳ ተጠቃሚዎች ገለጹ

61
ሐረር ኢዜአ መስከረም 4 ቀን 2012፡- የጤና መድህን ኢንሹራንስ አባል መሆናቸው በቀላሉ የህክምና አገልግሎት ማግኘት እንዳስቻላቸው በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ጉርሱም ወረዳ ተጠቃሚዎች ገለጹ። በዞኑ ከ188ሺህ የሚበልጡ አባወራዎች የጤና መድህን ኢንሹራንስ እየተጠቀሙ መሆናቸው ተመልክቷል። በጉርሱም ወረዳ የሙየዲን ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ አሊያ ኡስማን ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት የጤና መድህን መንግስት ገንዘብ ሊሰበስብበት እንጂ ለእነሱ አገልግሎት ሊሰጥበት እንዳልሆነ በሚል የተሳሳተ ግንዛቤ እንደነበራቸው አስታውሰዋል። “ከወረዳው ጤና ጽህፈት ቤት ጋር ባደረግነው ውይይት ግንዛቤ አግኝተን 250 ብር በመክፈል አባል መሆን ቻልኩ፤በዚህም ልጄ ለከፍተኛ ህክምና ወደ ሐረር ከተማ ላሳክም ችያለው” ብለዋል። ልጃቸው ለህክምና በተላከበት ወቅት ለምርመራ፣ለሆስፒታል አገልግሎትና ለመድኃኒት ያወጡትን 17ሺ ብር የመድህን ኢሹራንስ አባል በመሆናቸው በጤና ጽህፈት ቤት አማካኝነት እንደተመለሰላቸው ተናግረዋል። “የጤና መድህን አባልነት ከእኔ ባለፈ በተለይ በድህነት ውስጥ የሚገኙ አረጋዊያንና አቅመ ደካሞች ሲገለገሉበት ሳይ ቀደም ሲል የነበረኝ የተሳሳተ አመለካከት ተቀይሯል” ያሉት አቶ አህመድ ሻሚ ናቸው። እሳቸውም አባል በመሆን በድሬዳዋ ከተማ የከፍተኛ ህክምና አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰዋል። በተለይ አሁንም የአባላት መታወቂያ በሁሉም አካባቢ ከማዳረስና በአንዳንድ የጤና ቋማት ከሚታየው የመድኃኒት እጥረት ጋት ተያይዞ ተጠቃሚው  ቅሬታ እያሰማ በመሆኑ ሊስተካካል እንደሚገባ ጠቁመዋል። የሙየዲን ቀበሌ ገበሬ ማህበር የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኛ ወይዘሮ ሰላም ብርሃኑ እንዳሉት ለህብረተሰቡ በተሰጠው የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በቀበሌው ሁሉም አባወራ የጤና መድህን ኢንሹራንስ አባል ሆኗል። የአካባቢው ነዋሪው አገልግሎቱን በተግባር እያየ ተጠቃሚ በመሆን ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል። በጉርሱም ወረዳ ከሚገኙ 39ሺህ አባወራዎች ውስጥ 37ሺህ ያህሉ  የጤና መድህን ኢንሹራንስ አባል ማድረግ እንደተቻለ የገለጹት ደግሞ የወረዳው የጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብዲ ኡመር ናቸው። በዚህም ወረዳው በዞኑ ሞዴል ሆኖ መመረጡን ጠቅሰው በተያዘው አዲስ ዓመትም ቀሪዎችን አባወራዎችን ወደ ጤና መድህን ለማስገበት መታቀዱን አስረድተዋል። የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሀመዲን ከቢር ሁሴን በበኩላቸው ባለፉት ሁለት ዓመታት በተደረገው እንቅስቃሴ በ16 ወረዳዎች ውስጥ ነዋሪዎችን የጤና መድህን ኢንሹራንስ አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉን ተናግረዋል። የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ቁጥርም  ከ188ሺ በላይ አባወራዎች እንደሆኑ አመልክተዋል። በተለይ በተጠቃሚው ዘንድ ከአባልነት መታወቂያና ከመድሃኒት አቅርቦት ጋር በተያያዘ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ነው። በተለይ በተያዘው ዓመት ቀሪ አራት ወረዳዎችንና አራት የከተማ አስተዳደሮችን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰራም አብራርተዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም