በጌዴኦ ዞን ከ6 ሺህ በላይ ለሚሆኑ አርሶ አደሮች የስራ እድል ለመፍጠር ታቅዷል

48
መስከረም 3/2012 በጌዴኦ ዞን በተያዘው የበጀት ዓመት ከ6 ሺህ በላይ የሚሆኑ መሬት አልባ አርሶ አደሮችን የስራ እድል ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ። እቅዱን ለማሳካትም ከ75 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መያዙን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ገልጸዋል። ዋና አስተዳዳሪው አቶ ገዙ አሰፋ ለኢዜአ እንደገለፁት ዞኑ በዞኑ ከ15 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች መሬት አልባ ሲሆኑ ከ45 ሺህ የሚልቁት ደግሞ ከግማሽ ሄክታር በታች መሬት ያላቸው መሆኑ በጥናት ተለይቷል። ችግሩን ለማቃለልም በዞኑ የዘላቂ ልማት ፕሮጀክት መቀረጹን ገልጸው የመጀመሪያ ደረጃ ትግበራው በተያዘው የበጀት ዓመት እንደሚጀመር ጠቁመዋል። በመጀመሪያው ዙር ትግበራም ከ6 ሺህ በላይ መሬት አልባ አርሶ አደሮችን በንብ ማነብና እንስሳት እርባታን ጨምሮ በ17 ዘርፎች ወደ ስራ ለማስገባት መታቀዱን ተናግረዋል። ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ ከ75 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መያዙን የገለጹት ዋና አስተዳዳሪው ለተፈጻሚነቱም በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ አስረድተዋል። የተቀመጠውን ግብ ከማሳካት ጎን ለጎን የዞኑን ህዝብ መስረታዊ ጥያቄዎች ለመመለስ ሁሉም ባለደርሻ አከላት ርብርብ እንዲያደርጉ ጥሪ አስተላልፈዋል። በዞኑ ዲላ ዙሪያ ወረዳ የጎላ ቀበሌ ነዋሪ  አርሶ አደር ዲንቻ ጅግሶ ከአባታቸው የወረሱትን አንድ ሄክታር የቡና ማሳ ለስድስት ልጆቻቸው አከፋፍለው ማውረሳቸውን ገልጸዋል። የቀራቸው መሬት ጎጆ ቀልሰው የሚኖሩበት ስፍራ ብቻ በመሆኑ ኑሮን ለማሸነፍ ሌት ተቀን ቢደክሙም ኑሮ አልገፋ እንዳላቸው ጠቁመዋል። ችግሩ ተባብሶ ለከፋ ጉዳት ከመጋለጣቸው በፊት መንግስት በዘረጋው ዘላቂ ልማት ፕሮጀክት መታቀፋቸው በቀጣይ ሰርቶ ለመለወጥ ተስፋ እንዲኖራቸው ማስቻሉን ገልጸዋል። ሌላኛው አስተያየት ሰጭ አርሶ አደር አብዮት ጅሶ በበኩላቸው በፕሮጀክቱ በመታቀፋቸው ደስተኛ መሆናቸውን ጠቅሰው ሰርተው ለመለወጥም ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል። በተለይ አካባቢያቸው በጥምር ግብርና የሚተዳደር አርሶ አደሮች ያሉበት መሆኑን ተከትሎ የተለያዩ እጽዋቶችና ዛፎች በመኖራቸው በንብ ማነብ ስራ ላይ ቢሰማሩ ውጤታማ እንደሚሆኑ እምነታቸውን ገልጸዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም