በኮምቦልቻና ነቀምቴ ከተሞች ለተማሪዎች የቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ

70
መስከረም 3/2011 አርሂቡ የኮምቦልቻ ልማትና አንድነት ማህበርና በነቀምቴ ከተማ የሚገኘው የዳሎቻ የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋም በየአካባቢያቸው ለሚገኙ ችግረኛ ተማሪዎችና አረጋዊያን የቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ፡፡ ማህበሩና ተቋሙ ለተማሪዎቹ የትምህርትና ለአረጋውያን ደግሞ የተለያዩ ቁሳቁሶችን ድጋፍ ያደረጉት ከ232 ሺህ ብር የሚበልጥ ወጪ በማድረግ ነው፡፡ በተለይ አርሂቡ የኮምቦልቻ ልማትና አንድነት ማህበር በኮምቦልቻ ከተማ የትምህርት ቁሳቁስ መግዛት ለማይችሉ 400 ተማሪዎችና አረጋዊያን የቁሳቁስ ድጋፍ ያደረገው ከ200 ሺህ ብር የሚበልጥ ወጪ በማድረግ መሆኑን የማህበሩ ኘሬዝዳንት አቶ እንድሪስ አራጌ ገልፀዋል፡፡ ህብረተሰቡን፣ ባለሃብቱ፣ ነጋዴዎችን፣ ፋብሪካዎችንና ሌሎችንም በማስተባበር ለተማሪዎች ሙሉ የትምህርት ቁሳቁስና ለ100 አረጋዊያን የብርድ ልብስ፣ የአንሶላና የተለያዩ ቁሳቁሶች ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡ የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ሴቶች ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሪት ዘሪቱ ሁሴን በበኩላቸው ማህበሩ ያደረገላቸው ተማሪዎችና አረጋዊያን የነበረባቸዉን ከፍተኛ ችግር ከመቅረፉም ባለፈ ሌሎች ለልማት፣ ለሰላምና ለአንድነት እንዲሰሩ በር እንደሚከፍት አስታውቀዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በነቀምቴ ከተማ የሚገኘው የዳሎታ አሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋም ከ32 ሺህ 200 ብር በላይ ወጪ በማድረግ ለችግረኛ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል፡፡ የተቋሙ ባለሃብት አቶ ጌታቸው መኮንን በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት የትምህርት ፍቅርና ፍላጎት እያለቻው በገንዘብ እጦት ምክንያት የትምህርት እድል ያላገኙ ሕፃናትን መርዳት ከፍተኛ የህሊና እርካታ ይሰጣል፡፡ ባለሃብቱ በቀጣይም ለችግረኛ ተማሪዎች ተመሳሳይ ድጋፍ በማድረግ ብቁና አገር ተረካቢ ዜጋ ለማፍራት በሚደረግ ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለማበርከት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል። የምስራቅ ወለጋ ዞን ኦሮሞ ዴሞኪራሲ ፓርቲ ሃላፊ አቶ በሪሶ ተመስገን በድጋፍ አሰጣጡ ላይ ተቋሙ ለተማሪዎች ላደረገው ድጋፍ  ምስጋና አቅርበዋል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም