የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ ያለውን ጉዳት ለመቀነስ በሰውና በአካባቢ መካከል አዲስ መስተጋብር ያስፈልጋል ተባለ

120
መስከረም 2/2012 በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት እየጨመረ የመጣውን የብዝሃ ህይወት መጥፋት ለመታደግ በሰውና በተፈጥሮ መካከል አዲስ መስተጋብር እንደሚያስፈልግ የተባበሩት መንግስታት ሪፖርት አመለከተ። የተባበሩት መንግስታት የ2019 የዘላቂ ልማት ግቦችን የተመለከተ አዲስ ሪፖርት ዛሬ አውጥቷል። ሪፖርቱ የዘላቂ ልማት ግብ አጀንዳ ተግባራዊ ከተደረገ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገመገመ መሆኑም ተገልጿል። ድህነት ቅነሳ፣ ርሃብ፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የሃይል አጠቃቀም፣  ፍትሃዊነትና ተደራሽነትን የመሳሰሉት የዘላቂ ልማት ግቦች የሪፖርቱ የትኩረት አካላት ናቸው። የአለምን ህዝብ ደህንነት ማረጋገጥና ድህነትን መቀነስ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የ2030 ዘላቂ ልማት ግቦች መካከል ይጠቀሳሉ። ይህን ማሳካት የሚቻለው በሰዎችና በተፈጥሮ መካከል ያለውን መስተጋብር የሚያጣጥም አፋጣኝና መሰረታዊ እርምጃ ከተወሰደ ብቻ ነው ሲል ያስጠነቅቃል ዛሬ ይፋ የሆነው ይኸው የድርጅቱ ሪፖርት። በማህበራዊና ስርአተ ጾታ መካከል ያለውን ኢ-ፍትሃዊነት በመሰረታዊነት መቀነስም እንዲሁ ትኩረት እንደሚያሻው በሪፖርቱ ተጠቁሟል። ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የመጣው ለውጥ በማህበረሰብ ኢ-ፍትሃዊ ተጠቃሚነትና በአካባቢ መራቆት ምክንያት በከፋ ሁኔታ ወደኋላ ሊመለስ እንደሚችልም አስጠንቅቋል። በእያንዳንዱ ግለሰብና በዘላቂ ልማት ግቦች መካከል ያለውን መስተጋብር ማጤን ችግሩን ለመቀነስ እንደሚያግዝ ሪፖርቱ አስገንዝቧል። አሁን አለም እየሄደበት ያለው የልማት ስልት ለውጥ ቢያመጣም ድህነት፣ ኢ-ፍትሃዊነት፣ የብዝሃ ህይወት መጥፋትና ሌሎች ችግሮችን አስከትሏል። ይህንን ለመለመጥ የሰው ልጅ ፍላጎቱን ለማሳካት እየሄደበት ያለውን መንገድ መለወጥ እንደሚያስፈልግ  ሳይንቲስቶች ይመክራሉ። የምጣኔ ሃብት እድገት በአካባቢ ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት መቀነስ የዘላቂ  ልማት ግቦችን ለማሳካት ትኩረት መደረግ ካለባቸው ጉዳዮች መካከል መሆኑን ሪፖርቱ አትቷል። በድሃ አገሮች ጥራት ያለው የማህበራዊ አገልግሎትና መሰረተ ልማት ለማቅረብ ከፍተኛ እድገት  እንደሚኖር የገለጸው ሪፖርቱ  ከአካባቢ ጋር አጣጥሞ መሄድ እንደሚያስፈልግ ጠቁሟል። በአለም ላይ በአሁኑ ጊዜ ወደ2 ቢሊዮን የሚጠጋ ህዝብ በምግብ እራሱን እንዳልቻለ የሚነገር ሲሆን 820 ሚሊዮን ህዝብ ደግሞ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት አጋጥሞታል። በተቃራኒው 2 ቢሊዮን ህዝብ ከመጠን በላይ ለሆነ ውፍረት የተጋለጠ መሆኑም ይነገራል። በመሆኑም በማደግ ላይ ያሉ አገሮች በምግብ እራስን ለመቻልና የተመጣጠነ ምግብ እጥረትን ለመከላከል ጠንካራ የማህበራዊ ጥበቃን መገንባት ይገባቸዋል ተብሏል። የተመጣጠነ ምግብ ችግር የአለም ትኩሳት ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ እየሆነ በመምጣቱ በማደግ ላይ ያሉ አገሮችም ሆነ ያደጉት ትኩረት ሊሰጡት እንደሚገባ ነው የተገለጸው። ሌላው በሪፖርቱ የተጠቀሰው የሃይል አጠቃቀም ሲሆን በአለም ላይ ያለውን ክፍተት ለመሙላት ሽግግር ከሚያስፈልጋችው ዘርፎች አንዱ ነው ተብሏል። ለዚህም የአለም አንድ ቢሊዮን የሚጠጋ ህዝብ ከኤሌክትሪክ አቅርቦት ውጪ መሆኑን መሆኑ ተገልጿል። መረጃው እንደሚጠቁመው ከሳህራ በታች ባሉ አገሮች ከ3 ቢሊዮን ህዝብ በላይ ለምግብ ማብሰያነት በሚጠቀመው ግብአት ምክንያት ለብክለት የተጋለጠ ሲሆን ከዚህ ጋር ተያይዞ በሚመጡ ችግሮች በአመት 3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሰዎች ያለ እድሜያቸው ህይወታቸውን ያጣሉ። በመሆኑም ይህንን ክፍተት ለመሙላት በሃይል አጠቃቀም ላይ ታዳሽ ሃይልን ጨምሮ የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚገባ ሪፖርቱ አስቀምጧል። በሪፖርቱ መሰረት እንደ አሮፓውያን አቆጣጠር በ2050 ሁለት ሶስተኛው የአለም ህዝብ በከተሞች ይኖራል፤ በመሆኑም የከተሞችን ህይወት የተሻለ ለማድረግ ብዙ ጥረት ይጠበቃል። በተለይም በህዝብ ትራንስፖርት ጥራትና ሌሎች መሰረተ ልማቶች፣ በማህበራዊ አገልግሎትና በምጣኔ ሃብት ዘርፍ ብዙ ተግባር ማከናወን ይገባልም ተብሏል። የዘላቂ ልማት ግብን ለመተግበር የሚያግዙ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን፣ የሴቶች ቡድንና ሌሎች ተቋማትን ለማጠናከር፣ በህግና በማህበራዊ ዘርፎች የሚደረግ ማግለል እንዲቆም ሪፖርቱ አስቀምጧል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም