በቡራዩ ከተማ በፖሊስ ካምፕ ላይ ጥቃት አድርሰዋል በሚል የተጠረጠሩ 22 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለጸ

175
ኢዜአ መስከረም 2/2011 በቡራዩ ከተማ በሚገኝ የኦሮሚያ ፖሊስ ካምፕ ላይ የቦምብ ጥቃት አድርሰዋል በሚል የተጠረጠሩ 22 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለፀ። በቡራዩ ከተማ በሚገኝ የፖሊስ ካምፕ ላይ ትናንት በተወረወረ የእጅ ቦምብ ጥቃት በ9 ሰዎች ላይ ቀላል ጉዳት መድረሱን ከኦሮሚያ ክልል መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ ያስረዳል። በጥቃቱ ጉዳት ከደረሰባቸው ውስጥ አንዱ የፖሊስ አባል እዛው የህክምና ድጋፍ እንዲያገኝ ተደርጓል። ቀሪዎቹ ስምንቱ ደግሞ ለህክምና ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ሆስፒታል ተወስደዋል። ወደፖሊስ ሆስፒታል ከተወሰዱት ውስጥም አብዛኞቹ የህክምና ድጋፍ ተደርጎላቸው በመመለስ ላይ መሆናቸውንም ከቢሮው የተገኘው መረጃ ጠቁሟል። ትናንት ምሽት 1 ሰዓት ከ30 ላይ በተፈፀመው የቦምብ ጥቃት ጉዳት ከደረሰባቸው ውስጥ አንዷ በካምፑ ለሚገኙ የፖሊስ አባላት ምግብ አዘጋጅ መሆኗም ታውቋል። በአሁኑ ወቅትም በኦሮሚያ ፖሊስ ካምፕ ላይ ጉዳት በማድረስ የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየተጣራ መሆኑንም ነው ቢሮው ያስታወቀው። እስካሁንም 22 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም