የጎንደር ዩንቨርሲቲ የግእዝ ቋንቋ በመጀመሪያ ዲግሪ መስጠት ሊጀምር ነው

94
መስከረም 2/2012 የጎንደር ዩንቨርሲቲ የመጥፋት አደጋ የተጋረጠበትን የግእዝ ቋንቋ ለመታደግ በአዲሱ የትምህርት ዘመን በመጀመሪያ ዲግሪ የቋንቋ ትምህርት ለመስጠት መዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡ የዩንቨርሲቲው የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዘዳንት ዶክተር ካሳሁን ተገኘ ለኢዜአ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ የግእዝ ቋንቋ ባለቤት ብትሆንም ለቋንቋው ማደግና መስፋፋት የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ ነው፡፡ "በዚህም ሳቢያ ቋንቋው የመጥፋት አደጋ የተጋረጠበት ከመሆኑም በላይ በግዕዝ ቋንቋ የተጻፉ በርካታ የብራና መጻፍትን ለጥናትና ምርምር ስራ ለማዋል አልተቻለም "ብለዋል፡፡ ዘመናት የተሻገሩና በቋንቋው የተጻፉ ለዘመናዊ ህክምና ሙያ የሚያግዙ ፣ ምጣኔ ሀብታዊ፣ባህላዊና ታሪካዊ ፋይዳ ያላቸው በርካታ መጻህፍቶች በኃይማኖት ተቋማትና ገዳማት ተወስነው መኖራቸውን አመልክተዋል፡፡ ዩንቨርሲቲው እነዚህን ቁሳዊና መንፈሳዊ እሴት የያዙ  መጻህፍት ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገሩ ለማድረግ ስርዓተ ትምህርት ተቀርጾና መምህራን ተቀጥረው የግእዝ ቋንቋን ለማስተማር መዘጋጀቱን አስታውቀዋል፡፡ በትምህርት ዘመኑ 50 ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ዝግጅት መደረጉን ያመለከቱት ዶክተር ካሳሁን፤ትምህርቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚሰጠውም በኤክስቴንሽንና በክረምት መርሃ ግብሮች መሆኑን አስረድተዋል። ትምህርቱ ሰፊ ተቀባይነት እያገኘ ሲሄድ መደበኛ ተማሪዎችን ጭምር በቀጣይ በግእዝ ቋንቋ አሰልጥኖ ለማስመረቅ መታቀደን  አመልክተዋል፡፡ የጎንደር ዩንቨርሲቲ 87 የመጀመሪያ ዲግሪ፤ 158 ሁለተኛ ዲግሪና 29 የሶስተኛ ዲግሪ የትምህርት ፕሮግራሞች እንዳሉት ተገልጿል፡፡ በመደበኛ ፣በተከታታይና በክረምት መርሃ ግብሮች ትምህርታቸውን የሚከታታሉ ከ45ሺ በላይ ተማሪዎች በዩንቨርሲቲው ይገኛሉ፡፡          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም