በዓሉ የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት ሰላምና መቻቻልን በማጠናከር መከበር አለበት ተባለ

99
ሀረር ሰኔ 8/2010 የሀረር ምዕመናን በዓሉን  የተቸገሩ ወገኖችን  በመርዳት፣ ሰላምና መቻቻልን በማጠናከርና አንድነትን በማጎልበት እንደሚያሳልፉ  ገልጸዋል። 1439ኛው የኢድ አል ፈጥር /ረመዳን/ በዓል ዛሬ በሀረር ኢማም አህመድ  ስታዲዮም በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ተከበረ። የታላቁ የሀረር መስጂድ ጁምኣ ኢማም ሼህ ሙክታር ሐጂ ሙባረክ በበዓሉ ላይ  እንደተናገሩት እስልምና ሰላም፣ ፍቅርና የአንድነት፣ አብሮ የመኖርን ባህል የሚያጠናክር እምነት በመሆኑ ኢድ አልፈጢርን ስያከብሩ ምዕመናኑ የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳትና በመንከባከብ መሆን አለበት። እስልምናንና ህብረተሰቡን  ሽፋን በማድረግ የሀገሪቱን ልማትና ሰላምን ለማደናቀፍ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ሐይሎችን ተግባር የሃይማኖት አስተምሮ የማይቀበለው በመሆኑ ወጣቱ ሊከላከለው እንደሚገባም አሳስበዋል። ''ወጣቱም ከጥፋት ተልዕኮ እራሱን በማራቅ ሐይማኖቱ የሚያዘውን መልካም ተግባር ማከናወንና አንድነቱን ማጠናከር ይገበዋል'' ብለዋል። በስፍራው የተገኙት ሐጂ ነጋሽ መሀመድ  በሰጡት አስተያየት ''የእስልምና እምነት የሰላምና ተቻችሎ የመኖር ኃይማኖት በመሆኑ ሙስሊሙ ህብረተሰብ የተቸገረ ወገኑን፣ አሳዳጊ የሌላቸውን ህጻናት በመርዳትና በመደገፍ  በዓሉን ማሳለፍ ይጠበቅበታል'' ብለዋል። ኃይማኖቱ የሚያዘውን የመረዳዳትና የመደጋገፍ ባህልን በሚያሳይ መልኩ ከጎረቤቶች፣ ረዳት ከሌላቸው ህጻናትና ወገኖቼ ጋር በዓሉን በድምቀት አከብረዋለው ያለው ደግሞ ወጣት ሳዲቅ ናስር  ነው። የኃይማኖት እኩልነትና የእምነት ነፃነት በተረጋገጠበት አገር ላይ ወጣቱን በመጠቀም የራስን ጥቅም ለማስቀደም የሚሞክሩትን አካላት ወጣቱ ሊጠነቀቀውና ተግባሩን ሊያወግዝ  እንደሚገባም ገልጿል፡፡ የእስልምና ሐይማኖት ሥርዓትና አስተምህሮ በሚፈቀደው መሠረት የታላቁ የሀረር መስጂድ ጁምኣ ኢማም ሼህ ሙክታር ሐጂ ሙባረክ አማካይነት የሰላት ስግደት ስነ ስርዓት ተከናውኗል። በሶላት ስነ ስርዓቱም የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙራድ አብዱልሃዲና የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አብዱልማሊክ በከር የተገኙ ሲሆን  የስታዲየሙ ስነስርዓት በሰላም ተጠናቋል። በከተማው በሚገኘው ኢማም አህመድ ስታዲዮም በተካሄደው ሥነ ሥርዓት ላይም በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የእምነቱ ተከታዮች ተገኝተዋል፡፡              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም