የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ ክለቦች ቁጥር ወደ 24 አደገ

106
ጳጉሜ 6/2011  ከመጪው አዲስ ዓመት ጀምሮ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ ክለቦች ቁጥር ወደ 24 እንዲያድግ መወሰኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታወቀ። የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እንደ አዲስ ከተመሰረተበት ከ1994 ዓ.ም ጀምሮ በየአመቱ 16 ክለቦችን እያሳተፈ በየዓመቱ በሁለት ክፍል ተከፍሎ ውድድሮችን ሲያካሂድ ቆይቷል። ነገ ከምንቀበለው 2012 ዓ.ም ጀምሮ ግን በፕሪሚየር ሊጉ ውድድር ላይ የፎርማትና የተሳታፊ ክለቦች ቁጥር ላይ ለውጥ አድርጓል። በዚህም መሰረት  ከመጪው አዲስ ዓመት ጀምሮ የፕሪሚየር ሊጉ ተሳታፊ ክለቦች ቁጥር ወደ 24 እንዲያድግ መወሰኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል። በመሆኑም ሊጉ እያንዳንዳቸው 12 ክለቦችን በሚይዙ ሁለት ምድቦች ተከፍሎ ውድድሩ ይካሄዳል ተብሏል። ውሳኔው የተላለፈው ከቅርብ ግዚያት ወዲህ በስፖርት ሜዳዎች ላይ በሚስተዋሉት ፖለቲካዊ መንፈስ ያላቸው አጀንዳዎች ሳቢያ እየተፈጠረ ያለውን የስፖርታዊ ጨዋነት ችግር ለመከላከል በማሰብ መሆኑንም ነው ፌዴሬሽኑ የገለጸው። በውሳኔው መሰረት በ2011ዓ.ም በሊጉ ተሳታፊ የነበሩ 16ቱ  ክለቦች በ2012 ውድድር የሚቆዩ ሲሆን ከከፍተኛ ሊጉ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ያደጉት ሶስቱ ክለቦችም ተካተዋል። እንዲሁም ከሱፐር ሊግ ውድድር ከየምድባቸው 2ኛ ደረጃን ይዘው ያጠናቀቁ ሶስት ክለቦች፤ እንዲሁም ሶስተኛ ከወጡት የተሻለ ነጥብ ያላቸው ሁለት ክለቦች የሊጉ አካላት ይሆናሉ ተብሏል። ይህ ፎርማት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት ፌዴሬሽኑ እና የሊጉ ተሳታፊ ክለቦች ውይይት ያደርጋሉ ተብሎም ይጠበቃል። ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ መከላከያ፣ መቀለ ሰብአ እንደርታ፣ ጅማ አባ ጅፋር፣ ባህር ዳር ከተማ፣ ፋሲል ከተማ፣ ሽረ እንዳስላሴ፣ ሐዋሳ ከተማ፣ ሲዳማ ቡና፣ አዳማ ከተማ፣ ድሬደዋ ከተማ፣ ውልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ፣ ወላይታ ድቻ፣ ደቡብ ፖሊስና ደደቢት የፕሪሚየር ሊጉ ተሳታፊ ክለቦች እንደነበሩ ይታወቃል። ወልቂጤ ከተማ፣ ሃድያ ሆሳእና እና ሰበታ ከነማ ደግሞ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ያደጉ ክለቦች ናቸው። መቀለ ሰብአ እንደርታም የ2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የዋንጫ አሸናፊ ሆኖ ማጠናቀቁ የሚታወስ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም