በድሬዳዋ 1439ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል በደማቅ ሥነ-ሥርዓት ተከበረ

3070

ድሬዳዋ ሰኔ 8/2010 በድሬዳዋ 1439ኛው የኢድ አልፈጥር /ረመዳን/ በዓል በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ-ሥርዓት ተከበረ፡፡

ሙስሊሙ ህብረተሰብ ለሰላምና ለልማት እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንዲቀጥል የድሬዳዋ ከንቲባ ኢብራሂም ዑስማን ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ከሌሊቱ 11 ሰዓት ጀምሮ ከዋና ዋና የድሬዳዋ መንገዶች ፈጣሪውን በምስጋናና በዝማሬ በማወደስ ወደ ኢድ ሜዳ የተጓዘው የከተማዋ ሙስሊም ህብረተሰብ በዓሉን በታላቅ የሶላት፣ መንፈሳዊ መዝሙሮችና መንፈሳዊ ትምህርቶች አክብሯል፡፡

የድሬዳዋ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ዑመር ከድር  በበዓሉ ላይ እንደተናገሩት ሙስሊሙ ህብረተሰብ በረመዳን ወር ሲያከናውናቸው የነበሩትን የፆም፣ የፀሎት የተቸገሩትን የመርዳትና ከዘመድና ከጎረቤቶቹ ጋር ተካፍሎ የመብላት እሴቶችን ሁልጊዜም አጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡

”በዓሉ የተቸገሩትን በመርዳት፣ የታመሙትን በመጠየቅ ፣ የተራቆቱትን በማልበስ ሊከበር ይገባል”ብለዋል፡፡

በበዓሉ ላይ ተገኝተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ኢብራሂም ዑስማን በበኩላቸው ሙስሊሙ ህብረተሰብ  ለሀገሩ ሠላም፣ ልማትና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መጎልበት እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ አጠንክሮ መቀበል እንዳበት ገልፀዋል፡፡

በተለይ ወጣቱ በመንፈሳዊ ሕይወቱ ያካበታቸውን የመረዳዳት፣ የመከባበርና የመቻቻል እሴቶችን በመጠቀም ድህነትንና ኋላ ቀርነትን ለማስወገድ በሚከናወኑ ተግባራት ግንባር ቀደም ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የበዓሉ ተሳታፊ ከነበሩት መካከል ወጣት ሁሴን ያሲን በሰጠው አስተያየት ወጣቱ በሀገሪቱ ሰላምና ልማት እንዲረጋገጥና በልማቱም እኩል ተጠቃሚ እንዲሆን እየሰራ ይገኛል፡፡

”በተለይ በአሁን ሰዓት በሀገሪቱ እየተካሄደ በሚገኘው የለውጥ እንቅስቃሴ ወጣቱ ደስተኛ ነው” ብሏል፡፡

ሙስሊሙ ህብረተሰብ ወሩን በፆምና በፀሎት ከፈጣሪው ጋር በመገናኘት ምህረት፣ ሰላምና ፍቅር ሲለምን እንደነበር ያስታወሱት ደግሞ አቶ መሐመድ አሚን አማን ናቸው፡፡

”በቀጣይ ለሀገር ሰላምና ልማት መረጋገጥ ያለብንን ኃላፊነት ለመወጣት የጀመርነውን ጥረት አጠናክረን እንቀጥላለን” ብለዋል፡፡

ወይዘሮ አሻ አብዱላሂ በበኩላቸው በዓሉን ከክርስቲያን ጎረቤቶቻቸው ጋር በመሆንና የተቸገሩትን በማብላት ለማክበር መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡