አዲስ አመት ለአዲስ ትልም

283

ቀበኔሳ ገቢሳ (ኢዜአ)

እንኳን ለአዲሱ ዓመት በሰላም አደረሳችሁ! ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካ የመሸጋገሪያው ዕለት በየዓመቱ ቅዱስ ዮሐንስ እየተባለ ይጠራል፡፡ የዘመን መለወጫ፣ እንቁጣጣሽ፣ ሌላም መጠሪያ ስሞቹ ናቸው፡፡ በግእዝ ርእሰ ዐውደ ዓመትም ይባላል፡፡ ይህ በዓል የዓመት መጀመሪያ እንደመሆኑ መጠን በየዓመቱ የመጀመሪያ ወር በመጀመሪያው ቀን ይከበራል፡፡

በኢትዮጵያ ዘመን መለወጫ በመስከረም ወር የሚከበርበትን ምክንያት ሊቃውንቶች ሲያትቱ ብርሃን፣ ፀሐይ፣ ጨረቃ እና ክዋክብት የዓመት ዑደታቸውን በጳጉሜ ጨርሰው በመስከረም ወር ስለሚጀምሩ ነው ይላሉ፡፡ ያን ጊዜ ሌሊቱ ከቀኑ ጋር እኩል 12 ሰዓት ይሆናል፡፡ ዓመቱን ጠንቅቀው ሲቆጥሩትም 365 ቀናት ይሆናል፡፡

አዲስ ዓመት አዲስ ተስፋ የሚሰነቅበት፣ አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር የዕድሜያችን ቁጥር የሚጨምርበት ብቻ ሳይሆን በኑሮ ላይም አዎንታዊ ለውጥን ለማድረግ ዕቅድ ይዘን የምንነሳበትም ነው። አዝመራዉ እንዲያሸት፣ ዉጥን እንዲሳካ፣ የጠባው አዲስ ዓመትም ሰላምን፣ ጤናን፣ ፍቅርንና መግባባትን ሰንቆ እንዲያልፍ ምኞት የሚገለጽበት ጭምር ነው።

በአዲስ ዘመን ሀገርና ህዝብ በአዲስመንፈስ፣ በአዲስ ዕቅድና በአዲስ ተስፋ መጪውን ዘመን ይቀበሉታል፤ ከአሮጌው ዘመን በመማር ለአዲሱ አመት የተለያዩ ዕቅዶችን ያወጣሉ። መልካም ነገሮችን ይዘው ይነሳሉ። በዚያው በተሰጠው ዘመን ሁሉም ሥራውን ያከናውናል፡፡ አከናውኖም ያልፋል፡፡

ስለ አዲሱ ዓመት ሲነሳ አሮጌውን አመት መዘንጋት አይገባም። ምክንያት ወደኋላ ዘወር ብሎ ያሳለፍነውን በመፈተሽ የተከወነውን ለማድነቅ በዕቅድ ብቻ የቀረውን ወደ ተግባር ለመለወጥ ይበጃልና።

የሰነፈ ቢኖር ከብርታቱ በመለየቱ ተጸጽቶ ወደፊት ጠንክሮ ለመሥራት ታጥቆ ለመነሣት፣ ክፉ ሥራ ሠርቶ ፈጣሪን ያስቀየመ ቢኖር ንስሐ ገብቶ ወደ ፈጣሪው ቀርቦ ለመዘጋጀት፣ በሌሎች መበለጥ ተሸፍኖ የቆየ በመብለጥ ጎዳና ላይ ለመረማመድ የሚያስችል መንፈሳዊ ቅናት ቢያድርበት፣ የዘመን መለወጥን ያህል ልዩ አጋጣሚ አይገኝም። ዘመን የሰው ልጆች ተግባራቸውን በጊዜ እየለኩ ወደ ውጤት ለማምጣት ካልሆነም በመጪው ለማሻሻል ቃል የሚገቡበት ከፈጣሪ የተሰጠ ፀጋነው። ለዚህ ይሆን ዘመን ታዛዥ እንጂ አዛዥ አይደለም የሚባለው፡፡

አዲስ ዓመት በየዓመቱ የሚሰጠን ዕድል የትናንት ስህተታችንን እንድናርም፣ የተጣላን እንድንታረቅ፣ የበደልን እንድንክስ፣ የታረዘን እንድናለብስ፣ የተጠማን እንድናጠጣ፣ የተራበን እንድና በላ ከሁሉም በሚልቀው ፍቅር ተሞልተን በጎ በጎውን እንድናስብ ብሎም እንድንፈፅም ነው። የዘመኑ መቀየር ከቁጥር በዘለለ በእኛ ህይወት ውስጥ የተለየ ቦታ አለው፡፡

“አዲሱ ዓመት በመጽሐፉ ውስጥ ለመጻፍ በመጠባበቅ ላይ እንዳለ አንድ ምዕራፍ ከፊት ለፊታችን ቆሟል፡፡ አዲስ ዓመትን እየተቀበለ በአሮጌው አስተሳሰብ መሄድ ምኑን አዲስ ዓመት ነው? ፊትን ወደ ትናንት አዙሮ እንዴት ነው ወደ ነገ መጓዝ የምንችልው?” እንዳሉት ጠቅላይ ሚኒስተር አቢይ አህመድ። ሆኖም፣ ስለአዲስ ዓመት ስንናገር የሰው ልጅ በአዲስ አመት የተሻለ ደረጃ ለመድረስ ያቅዳል፣ ያስባል። የአዲስ አመት ዕቅድ ማለት ሰዎች በአዲስ አመት የተሻሉ ለመሆን ለራሳቸው የሚገቡት ቃል ነው፡፡

የአዲስ አመት ዕቅድ አንድ ሰው አንድ ጥሩ ነገር ለመሥራት ወይም መጥፎ ባህሪን ለማረቅ ለራሱ የሚገባው ቃልም ነው። ዕቅዱ ሰዎች በመጪው ዘመን ስኬታማ ትዳርን ለመመስረት፣ ከተጣቧቸው ሱሶች (የሲጋራን ጨምሮ) ለመላቀቅ ዕቅድ የሚይዙበት ነው። ዞሮ ዞሮ ሰው ቢያቅድ ህይወቱን መልካም እና የተሻለ ለማድረግ ነውና ለሰዎችም መልካም ሆኖ መገኘትንም መዘንጋት አይኖርበትም። ከሲጋራ ሱስ ስለመላቀቅ ሲነሳ አንድ ጓደኛዬ ያጫወተኝ ታሪክ ወይም ቀልድ ትዝ አለኝ። ‘ልጁ በአዲሱ አመት ሲጋራ ማጨሱን ለማቆም በማቀድ ቃል ይገባል። ከዚያም ጓደኛዬ በጓደኛው ከሱስ የመላቀቅ ዕቅድ እጅጉን ይደሰታል። ከዚያም አዲሱ አመት ይነጋና ጓደኛዬ ለበኣል የሚያዘውን ይዞ ዘመዱን ለመጠየቅ ወደ ታክሲ ተራ በሚያመራበት ወቅት ቃሉን ያጠፈው ጓደኛው አንዲት ኪዮስክ ሱቅን ተደግፎ ሲጋራ ሲያጨስ ያገኘዋል። በዚህ ጊዜ ጓደኛዬ ተገርሞ ‘አንተ ሲጋራ ለመተው ቃል ገብተህ አልነበረም እንዴ!’ቢለው እሱም ቀበል አድርጎ “አባቴ ይሙት!! ትናንት የተለኮሰ ሲጋራ ነው” ሲል መለሰለት ሲል ሳቄን መቆጣጠር አቅቶኝ ነበር። ይህ ሰዎች ለራሳቸው የገቡትን ቃል ማክበር ሲሳናቸው ለድክመታቸው ምክንያት እንደማያጡ አንዱ ማሳያ ሊሆን ይችላል።

የአዲስ አመት ዕቅዶች ብዙውን ጊዜ በተለያየ ሁኔታ ሊታቀዱ ይችላሉ፡፡ አንዳንድ ሰዎች ማጨስን ማቆም ወይም ከመጥፎ ልማዶቻቸው ለመውጣት ቃል ይገባሉ፡፡ ሌሎች ሰዎች ደግሞ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መርሃ ግብር ለመጀመር፣ የሥራ ዘርፍን ለመቀየር ወይም ማህበረሰብን በበጎ ፈቃደኝነት ለማገልገል እና መልካም ልምድን ለማዳበር ቃል ይገባሉ። ችግሩ ቃል የመግባት ሳይሆን ቃልን አክብሮ ራስን መለወጥ ላይ የሚታዩ ቸልተኝነቶች የሚያመጧቸው አሉታዊ ውጤቶች ናቸው። ቃልን አክብሮ ላለመገኘት የሚሰጡ ምክንያቶችም ከላይ በቀልድ መልክ የቀረበውን ታሪክ አይነት ሁኔታ ውስጥ እንድንገባ ሊያደርገን ይችላል። ስለሆነም የአዲስ አመት ዕቅድን ወደ ተግባር ለመለወጥ መጣር እና ለቃላችን መታመን ደግሞ ከእኛ ይጠበቃል።

ብዙዎቻችን ህይወታችንን ለመለወጥ ወደ አዲስ ዓመት እንገባለን፣ ነገር ግን ከዓመት ወደ ዓመት ምንም የተለወጠ ነገር አናገኝም፡፡ አንዳንድ ሰዎች በአዲስ ዓመት የተሻሉ ለመሆን ወይም ለመለወጥ ቃል ይገባሉ፡፡ ግን ፣ በመስከረም ወር ከታቀደው ዕቅድ ውስጥ የተወሰነው የሚሆነው በጥቅምት ወር ሳይሳካ ይቀራል ።ለአዲሱ ዓመት ያቀዷቸው እቅዶች ካልሰሩ ወይም ካልተሳኩ ወደ ዕቅድ ሰሌዳው መመለስ ሊኖርብዎ ይችላል። ይህ ማለት የእርስዎ ዕቅድ ወይም ዘዴ አይሠራም ማለት ነው፤ ስለዚህ የተዘጋጀውን እቅድ እንደገና በመፈተሽ ለችግሩ አዲስ መፍትሄ ማዘጋጀት ይኖርብናል ማለት ነው፡፡

ስለዚህ ስንቶቻችን ነን በአዲስ አመት የተሻለ ለመሆን የተዘጋጀ ነው? ባለስልጣኑም ህዝቡን ለማገልገል፣ የህግ ባለሙያውም ሚዛናዊ ፍርድ ለመስጠት፣ ቤተ ዕምነቶችም ለህዝቦች መልካሙን ነገር ለማስተማር፣ አሸባሪውም ሰላማዊ ለመሆን፣ መሀንዲሱም ቀና ጎዳናዎችን ለመቀየስ፣ ሸማኔውም የተነጠለውን ለመደረብ እና የተለያየውን ለመስፋት ደራሲዉ እና ጋዜጠኛውም ገለልተኛ በመሆን እውነትን ለመናገር፣ ሀኪሙም በሽተኛውን ለማከም እና ገበሬውም መልካሙን ፍሬ በለም መሬቱ ላይ ለመዝራት በአዲስ አመት ይዘጋጃል።

እኛ ፍቅር ስንሆን ዘመኑ የፍቅር ይሆናል እኛ ሰላማዊ ስንሆን ዘመኑ የሰላም ይሆናል ከዚህ በተመሳሳይ ደግሞ ለምንም ነገር የማንበገር ብርቱ ሰራተኞች ስንሆን ዘመኑ የብልጽግና ይሆንልናል!! እያንዳንዱ አዲስ ዓመት ቅዱስበረከቶችን ያመጣልና የመልካሟ ኢትዮጲያ ልጆች ኑ የተሻለ ዘመን እንፍጠር። መልካም አዲስ አመት!!